የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኮቲዲቫር ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይካሄዳል ተባለ

60
ኢዜአ ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኮቲዲቫር ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንዲካሄድ መወሰኑን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታወቀ። ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ስታዴየሞቿን ካላስተካከለች የአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታውን በጎረቤት ሀገራት እንዲያካሄድ ይደረጋል ሲልም ካፍ አስጠንቅቋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሁለት ዓመት በኋላ በአውሮፓዊያን 2021 ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኮቲዲቯር፣ ኒጀርና ማዳስካር ጋር መደልደሉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ከማዳስካር ጋር ያካሄዳል። ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ደግሞ ከኮቲዲቫር ጋር  መቀሌ ስታዴየም ላይ ለማካሄድ ታስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ  ውድድር  ለማስተናገድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የለውም በሚል የቦታ ለውጥ ተደርጎ ጨዋታው ባህርዳር ስታዲየም እንደሚካሄድ ካፍ በደብዳቤ አስታውቋል። የባህርዳር ስታዲየምም ቢሆን ካፍ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ለማሟላት ከወዲሁ ጥረት የማያደርግ  ከሆነ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ጎረቤት ሀገራት ለማድረግ ትገደዳለች ሲልም ካፍ አስጠንቅቋል። የካፍ የልህቀት አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ ተድላ ዳኛቸው ለኢዜኣ እንደገለጹት ሰሞኑን ከካፍ በመጡት ባለሙያዎች የተለያዩ የአገሪቱ ስታዲየሞች ተገምግመዋል። ከተገመገሙት ስታዲየሞች መካከል  የባህርዳር ስታዴየም ብቻ ዓለም አቀፍ ውድድር እንዲያስተናገድ ተመረጠ የተባለው መረጃ ግን ስህተተ መሆኑን ነው አቶ ተድላ የተናገሩት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአገሪቱ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም አላቸው በሚል ያቀረባቸውን የወልዲያ፣ የመቀሌና የባህርዳር ስታዴየሞችን ባለሙያዎቹ ተመልክተዋል። በባለሙያዎቹ የተካሄደው ይህ ግምገማ ውጤት ይፋ የሚደረገው ገና ወደፊት መሆኑንም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መቀሌ ላይ ከኮቲዲቯር ጋር ያከናውነዋል ተብሎ የነበረው ጨዋታ ወደ ባህርዳር የዞረውም ሰሞኑን በተካሄደው የካፍ ግምገማ መሰረት እንዳልሆነም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋልያዎቹ ከኮቲዳቫር ጋር በመቀሌ ሊያደረጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ባህርዳር እንዲዘወዋር የተደረገው ሰሞኑን አንድ የካፍ ባለሙያ  ለካፍ በሰጡት አስተየያት ነው ብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም