ምክር ቤቱ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል ህግ የማስከበር ስራ መጠናከር እንዳለበት አሳሰበ

53
ኢዜአ ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም በከተሞች እየተስፋፋ የመጣውን ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ለመከላከል አሰራሮችን ማሻሻልና ህግ የማስከበር ስራውን ማጠናከር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑን የሁሉም ትብብር ያስፈልጋል ብሏል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን የ2012 በጀት የሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ እንዳሉት፤ መሬት የዜጎች ዋነኛ ሃብት በመሆኑ በተለይ በከተሞች አካባቢ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ከባድ እክል እየፈጠረ መጥቷል። በኢትዮጵያ የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ በመጣው የቤቶች ግንባታና መሰረተ ልማት እድገት የመሬት አቅርቦቱና ፍላጎቱ እየተጣጣመ አለመሆኑንም ገልጸዋል። የሊዝ አዋጁን ጨምሮ የተለያዩ መሬት ነክ የአሰራር ማነቆዎች ዜጎች በከተማ መሬት ለማግኘት ሲጠይቁ በአግባቡ እየተስተናገዱና ምላሽ እያገኙ አይደለም ብለዋል። የሊዝ ህጉ ዜጎች በዓመት አራት ጊዜ መሬት እንዲቀርብላቸው ቢያስገደድም መንግስት ግን አንድም ጊዜ የማያቀርብበት ወቅት እንዳለም ጠቅሰዋል። በዚህም በርካታ ዜጎች የከተማ መሬት ለማግኘት ሲሉ የሚፈጠረውን ቢሮክራሲ በመፍራት በአቋራጭ ህገ ወጥ መንገድን መከተል ምርጫቸው ያደርጋሉ። የሊዝ አዋጁ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች ስላሉት እንዲሻሻል በተወሰነው መሰረት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አዋጁን በፍጥነት አዘጋጅቶ ማቅርብ እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገ ወጥ መሬት ወረራን ለመከላከል በቅርጅት መስራትን ይጠይቃል። አዲስ የሊዝ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተፈትሾ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል። ህግ የማስከበር ስራ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለደርሻ አካላት ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ በትብብር መስራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም