ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲጠናከር ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው---ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

114
ጎንደር  ህዳር 3 / 2012 ---በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሰላምን ለማጠናከር ከሃይማቶች አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከሰላምና ልማት ሸንጎና ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንቱ ዶክተር አስራት አጸፈወይን ለኢዜአ እንዳሉት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የተፈጠረው ግጭት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ተቋሙ ለተማሪዎች ደህንነት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ በተለይ የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም፣ አንድነትና ወንድማማችነት በዩኒቨርሲቲው በቋሚነት ትምህርት የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል። ከከተማው የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ጋር የምክክር መድረኮችን በማመቻቻት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲጠናከር እየሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን በመስራት በኩል ከአጋር አካላት ጋር ውይይት መደረጉን የጠቆሙት ዶክተር አስራት፣ "ለትንኮሳና ለግጭት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን ፈጥኖ ለማረምና ለማስተካካል እንዲቻል አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል" ብለዋል። ልዩ ልዩ የተማሪ አደረጃጃቶችን ከመፍጠር ባለፈ ተማሪዎች ለሚገጥማቸው ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአሰራር ስርአት ተግባራዊ መደረጉንም አስረድተዋል። ዘንድሮ ወደዩኒቨርሲቲው የተቀላቀሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ከከተማው ህብረተሰብ ጋር በቅርበ ቤተሰባዊ ትስስር እንዲኖራቸው የተጀመረው የቤተሰብ ፕሮጀክትም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡ "የቤተሰብ ፕሮጀክቱ 5 ሺህ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው አዲስ ገቢ ተማሪዎች እያንዳንዳቸው አንድ የቅርብ ቤተሰብ እንዲኖራቸው በማድረግ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያገዘ ነው" ብለዋል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ከሁለት ሳምንት በፊት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግጭት እንደተቀሰቀሰ ተደርጎ የተለቀቀው መረጃ ሀሰተኛ ስለመሆኑ ተከታትለው ማጋለጠጫቸውን የገለጹት ዶክተር አስራት፣ "በቀጣይም የማጋለጡን ስራ እንቀጥላለን" ብለዋል። በወቅቱ ወላጆች ከተማሪዎች ጋር በስልክ አነዲገናኙ በማድረግ ወሬው ሆን ተብሎ የተለቀቀ ሀሰተኛ መሆኑን እንዲገነዘቡ መደረጉንም አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች ፍጹም ሰላም የሰፈነበት የመማር ማስተማር ሂደት መኖሩን ፕሬዘዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመደበኛና በማታው የትምህርት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን እየተከታታሉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም