በእንዳመኾኒ ወረዳ የአቅመ ደካሞችና የአረጋዊያን ሰብል በዘመቻ ተሰበሰበ

56
ማይጨው (ኢዜአ) ህዳር 02 ቀን 2012 ዓ.ም በትግራይ ደቡባዊ ዞን እንዳመኾኒ ወረዳ የአቅመ ደካሞችና የአረጋዊያን የደረሰ ሰብል በተማሪዎችና በከተማ ወጣቶች ድጋፍ እንዲሰበሰብ ተደረገ። ሰብላቸው የተሰበሰበላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው፣ ድጋፍ ሰብላቸው ከአንበጣ መንጋና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ከመጎዳት እንደታደጋቸው ተናግረዋል። ሰብሉ ጉዳት ሳይደርስበት በወቅቱ እንዲሰበሰብ የተደረገው በማይጨው ፖሊ- ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎችና በከተማው ወጣቶች ትብብር ነው። የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ አሰፋ አስረስ እንደገለፁት፣ በእንዳመሆኒ ወረዳ በመካንና በሑጉምብርዳ ቀበሌዎች በተደረገው የሰብል መሰብሰብ ሥራ ላይ ከ450 በላይ ተማሪዎችና ወጣቶች ተሳትፈዋል። በሰብል ስብሰባ ዘመቻ ስራው በሁለቱም ቀበሌዎች ከ35 በላይ አቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ በ22 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብልም ሊሰበሰብ ችሏል። የማይጨው ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን መምህር ግርማይ ሓጎስ በበኩላቸው፣ ባለፈው ሳምንት በወረዳው ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ በማስወገድ ዘመቻ ላይ የተሳተፉ የኮሌጁ ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት የአርሶ አደሮችን ሰብል በመሰብሰብ የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። "የኮሌጁ 150 ተማሪዎችና መምህራን መካን የገጠር ቀበሌ በመገኘት የአራት ሴት አርሶ አደሮችን ጨምሮ የ13 አርሶ አደሮች ሰብል አጭደው ሰብስበዋል" ብለዋል። የኮሎጁ ተማሪዎች ለአንድ ሳምንት ወደመጡበት አካባቢ በመሄድ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙ የሚደረግ መሆኑንም አመልክተዋል። በወረዳው ውስጥ ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ በማስወገድ ዘመቻ መሳተፋቸውን የገለጹት ተማሪ አሌክሳንደር ስዩምና ትዕግስት ንጉስ፣ የአቅመ ደካሞችንና የአረጋዊያንን ሰብል በመሰብሰባቸው የህሊና እርካታ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው አርሶ አደሮች በበኩላቸው፣ ሰብላቸው በመሰብሰቡ የአንበጣ መንጋና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት ያደርስብናል ከሚል ስጋት እንደታደጋቸው ነው የገለጹት። "ሰብሌን ሠራተኛ ቀጥሬ እንዳላሰበስብ አቅም የለኝም፤ ከነገ ዛሬ አንበጣ መጣ ዝናብ ሊዘንብ ነው እያልኩ ስጋት ገብቶ ነበር" ያሉት ደግሞ ሰብላቸው የተሰበሰበላቸው ወይዘሮ አክላ ደበሳይ። "ወጣቶች ሰብሌን በመሰብሰብ እገዛ ስላደረጉልኝ ከስጋት ነፃ ሁኛለሁ" ብለዋል ወይዘሮ አክላ። "ግማሽ ሄክታር በሚጠጋ ሰብሌ ላይ የለማ የስንዴ ሰብል በአንበጣ ሊበላብኝ ነው እያልኩ በሰጋሁበት ወቅት ተማሪዎች የዓመት ቀለቤን ስለሰበሰቡልኝ በጣም ደስተኛ ነኝ " ያሉት ደግሞ ሌላኛው የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጎደፋ ዓለም ናቸው።    
   
 
   
           
   
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም