የመደመር እሳቤ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለብሄራዊ ጥቅም፣ ክብር እና ለጎረቤት አገሮች ልዩ ትኩረት ይሰጣል

72
ኅዳር 3/2012 የመደመር እሳቤ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለብሄራዊ ጥቅም፣ ክብር እና ለጎረቤት አገሮች ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን አንድ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምሁር ተናገሩ፡፡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስራኤልና የስዋዚላንድ አምባሳደሮችም “መደመር” ከኢትዮጵያም ባለፈ ከሌሎች አገሮች ጋር ለሚኖረው አብሮነት አዲስ አስተሳሰብ ይዞ ብቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል። መደመር በፖለቲካና ኢኮኖሚው መስክ የሚያስተጋባቸውን ፉክክርና ትብብር አስታርቆ የመጓዝ ጥበብና መላ በውጭ ግንኙነቱም ይከተላል። ከትናንት የተወረሱ መልካም እድሎችን ጠብቆ ማቆየትና በተጓዳኝ የነበሩ ስህተቶችን በማረም ለመፃኢው ትውልድ የበለፀገች ኢትዮጵያን ማስረከብ ይሻል። በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተንታኝ አቶ መሀመድ ራፊያ አባራያ የመደመር እሳቤ የውጭ ግንኙነትን በሚመለከት የትኛውንም አገር በወዳጅነትና በጠላትነት እንደማይፈርጅ ይገልጻሉ። ለብሄራዊ ጥቅም እንዲሁም ብሄራዊ ክብር ከግለሰብ ጀምሮ እንደ አገር ልዩ ትኩረት የሚሰጥ አዲስ እሳቤ ነው። አዲሱ እሳቤ ካለፈው መልካም ተሞክሮ በመቀመር ማስቀጠል እንዲሁም ስህተቶችን በማረም ለስኬት ጥረት እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። እሳቤው ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የነበራትን ሚና አጠናክሮ የሚያስቀጥልና በዜጎች ክብርና ነፃነት ዙሪያ የነበረውን ክፍተት ማሻሻል እንደሚገባ የሚያምን መሆኑን ገልጸዋል። መደመር በውጭ ግንኙነት መስክ ለጎረቤት አገሮች ቅድሚያ በመስጠት በትብብርና በጋራ ለመስራት ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን አቶ መሃመድ ተናግረዋል። በቀጠናው በርካታ የልማትና የእድገት አማራጮች ያሉበት መሆኑን በማመን “ከስጋት ይልቅ” በምጣኔ ሃብት ትብብርና ውህደት ያምናል። ከጎረቤት አገሮች ጋር ከጥንት ጀምሮ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የታሪክ፣ የቋንቋና የባህል ትስስር መኖሩን በማመን ይበልጥ ማጠናከርን ታሳቢ እንደሚያደርግ አቶ ሙሀመድ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የስዋዚላንድ አምባሳደር ፕሮሚሴ ሚሲቤ እንደሚሉት “መደመር“ ለመላ አፍሪካ ሊጠቅም የሚችል አዲስ አስተሳሰብ ያስተዋሉበት ነው። በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፌል ሞራቭ በበኩላቸው “መደመር” ለብዝሃነት አዲስ ጠቃሚ ሃሳብ ይዞ ብቅ ያለ መሆኑን ተናግረዋል። እሳቤው ለመላ አፍሪካና አጠቃላይ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠቃሚ ሃሳብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ይላሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም