በቦረና ዞን 23 ሺህ 200 ስራ አጥ ወጣቶች ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው

60

ነገሌ ኢዜአ ህዳር 3/2012  በቦረና ዞን 23 ሺህ 200 ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት 48 ሚሊዮን ብር የብድር ገንዘብና የመስሪያና የመሸጫ ቦታ መዘጋጀቱን የዞኑ ምግብ ዋስትናና የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የስራ እድል ፈጠራ ባለሙያ አቶ አጥናቸው ቶልቻ እንደገለፁት የዞኑ ወጣቶች የብድር አገልግሎት ፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ችግር በተመለከተ በየጊዜው ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር  አስታውሰዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ከባለድረሻ አካላት ጋር በመነጋገር 4 ሱቅ ፣ 9 ሺህ 600 ካሬ ሜትር የመስሪያ ቦታና 48 ሚሊዮን ብር ብድር መመቻቸቱን ጠቁመዋል፡፡

በመንግስት የተቀመጠውን ህጋዊ አሰራር ተከትለው የተደራጁና ጥያቄ ያቀርቡ ወጣቶችና ማህበራት ተራቸውን ጠብቀው በፍትሀዊነት ይስተናገዳሉ ብለዋል፡፡

በቦረና ዞን በገጠርና በከተማ በዚህ አመት 23 ሺ 200 ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 18 ሚሊዮን ብር ብድር የወሰዱ 2 ሺህ 447 ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶቹ ወደ ስራ የገቡት በግንባታ ፣ በኢንዱስትሪ ፣ በግብርና ፣ በአገልግሎትና በንግድ ዋና ዋና የስራ ዘርፎች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ተልተሌ ወረዳ በብረታ ብረት ሙያ ወደስራ የገባው ወጣት ጎዳና ጂሎና 5 ባልደረቦቹ 75 ሺህ ብር ብድር መውሰዳቸውን ገልጿል፡፡

የብድር አቅርቦት በመመቻቸቱ ለተጠቃሚዎች ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ሰርተው ለመለወጥ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆኑ ተናግሯል ፡፡

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ሰለሞን ወንድሙ በበኩሉ የብድር አገልግሎት ቢመቻችም የመብራት መቆራረጥና የገበያ ትስስር ችግር አሁንም አልተፈታም ብሏል ።

መሰረተ ልማት በማሟላት ወጣቱን ወደ ስራ በማስገባት ማህበራዊ ችግሮቹን ለማቃለል በቃል የሚገለጸው ተስፋበተግባርም እንዲታይ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም