አየር መንገዱ የሼባ ማይልስ ደንበኞቹን 20ኛ ዓመት ክብረ በዓል አከበረ

74
ህዳር 3/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሼባ ማይልስ ደንበኞቹን 20ኛ ዓመት ክብረ በዓል አክብሯል። አየር መንገዱ ከ1 ሺህ አምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ የሼባ ማይልስ ታማኝ ደንበኞቹ ትናንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል የእራት ግብዣና የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር አካሂዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ ተዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በዝግጅቱ ላይ የሼባ ማይልስ ፕላቲኒየም አባላት የሆኑና የካርጎ ተጠቃሚ ደንበኞች ለአየር መንገዱ ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና ተሰቷቸዋል። የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በዝግጅቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ "በዓመታት ውስጥ ለደንበኞቻችን ተጨማሪ በርካታ መዳረሻዎችን ማቅረብ በመቻላችን ደስታ ይሰማናል" ብለዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ "ለአየር መንገዱ ስኬታማ ጉዞ ደንበኞች ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል" ያሉት አቶ ተወልደ ከበርካታ አየር መንገዶች ጋር በተፈጠረ ስምምነት "ርቀቶችን በማቅረብ አለም አቀፍ ተመራጭ አየር መንገድ ለመሆን በቅተናልም" ብለዋል። አየር መንገዱ የእነዚህን ታማኝ ደንበኞቹን ፍላጎት የበለጠ ለማርካት በቀጣይ የተለያዩ የአገልግሎትን ማዘመኛ ስራዎችን  እንደሚሰራ ገልፀው የአየር መንገዱ ደንበኞች ለዓመታት  እያደረጉት ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና ችረዋል። ሼባ ማይልስ ስያሜውን ያገኘው የኢትዮጵያዋ ንግስተ ሳባ ለንጉስ ሰለሞን የለገሰችውን ስጦታ ታሳቢ ተደርጎ ሲሆን  አየር መንገዱ ሼባ ማይልስ የደንበኞች አገልግሎት መስጠት የጀመረው በፈረንጆቹ የካቲት 1999  ነው። በወቅቱ በ300 አባላት የሼባ ማይልስ አገልግሎትን መስጠት የጀመረው አየር መንገዱ አሁን ላይ በ110 አገራት ያሉ ከ3 ሚሊየን በላይ  የሼባ ማይልስ አባላትን ማቀፍ ችሏል። አየር መንገዱ 12 ሚሊየን መንገደኞችን በዓመት የሚያጓጉዝ ሲሆን ባለፈው 2011 ዓመትም 4 ቢልየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አስገብቷል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም