በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትምህርት፣ ውሃና ጤና ዘርፍ የሚጠበቀውን ያህል ስኬታማ አልሆኑም

66
ህዳር 2/2012 በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በትምህርት፣ ውሃና ጤና መሰረታዊ አገልግሎት ልማት በሚጠበቀው ልክ ስኬታማ አለመሆኑ ተገለጸ። ለሶስቱም የመሰረታዊ አገልግሎት ዘርፎች ግቦች አለመሳካት አገራዊ የጸጥታ ችግሩ አሉታዊ አስተዋጽኦ አንደነበረው ተመልክቷል። የገንዘብ ሚኒስቴር፣ በመሰረታዊ አገልግሎት ዘርፍ ከሚሰሩ የፌዴራልና የክልል ተቋማትና ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅት ተወካዮች ጋር በመሆን ለሶስት ቀናት የሚቆይ የመሰረታዊ አገልግሎትን የሚመለከት የጋራ ግምገማ መድረክ እያካሄደ ነው። ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በየዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ግምገማ የራሱ መለኪሚያዎች የተቀመጡለት እንጂ እንደቀድሞው ጊዜ በዘፈቀደ ሪፖርት የሚቀርብ ባለመሆኑ የሚቀርበው መረጃ ጥራት ያለው መሆኑን ገልጸዋል። በዛሬው የግምገማ መድረክም ላለፉት አራት ዓመታት በትምህርት፣ በጤናና በውሃ ሀብት ልማት ዘርፍ በአንዳንዱ ጥሩ አፈጻጸም መኖሩን፣ በሌላው ግን ወደኋላ የቀረ አፈጻጸም መኖሩን አብራርተዋል። የመሰረታዊ አገልግሎት ጥራት ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ ላቀደችው ግብ አንዱ መለኪያ መሆኑን በመግለጽ፣ ግምገማውም አሁን ካለበት ወደፊት እንዴት እንራመድ ለሚለው ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል። በትምህርት ሚኒስቴር የዕቅድ ዝግጅትና ሀብት ማፈላለግ ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ግርማም በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በትምህርት ዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም በርካታ ግቦችን ማሳካት መቻሉን አውስተዋል። ለአብነትም በትምህርት ተደራሸነት፣ በሴቶች ተሳትፎ፣ የመምህራንን ጥራት በማሻሻል፣ የትምህርት በጀት በማሳደግና በስርዓተ ትምህርት ስርጭት ረገድ ውጤት ያሳካንባቸው መስኮች ናቸው ብለዋል። ይሁንና በቅደመ መደበኛ ትምህርት ተደራሽነት፣ በተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት፣ ከክፍል ክፍል በመዘዋወር ብቃት፣ በመጠነ ማቋረጥና መጠነ መድገም ረገድ በዕቅዱ የተመላከቱ ግቦች አልተሳኩም ብለዋል። በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አገራዊ ችግሮች እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች 'በአጠቃላይ ሲታይ በተለይም በትምህርት ጥራትና ውስጣዊ ብቃትን ከማረጋገጥ አኳያ ውጤታማ ነን ብለን አልገመገምንም' ብለዋል። በቀጣይ የሚተገበረው የትምህርት ፍኖተ ካርታው ዓላማም እነዚህን ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። በጤና ሚኒስቴር የፖሊሲ ዕቅድ ክትትል ግምገማ ዳይሬክትሬት የጤና መረጃ ስርዓት አማካሪ አቶ ጋዲሳ ለሜቻ በበኩላቸው በጤናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ በተቀመጡ ግቦች የደረስንባቸው የተወሰኑት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ዓመት የተቻለውን ያህል ጥረት እንደሚደረግ ገልጸው፤ በዕቅድ የማንደርስባቸውን ግን በቀጣይ ዕቅዶች ለመስራት ታሳቢ እንደሚደረጉ አብራርተዋል። ለአብነትም በክትባትና በወሊድ ክትትል ዘርፍ ጠቅሰው፤ በወሊድ ክትትል ተደራሽነት 95 ከመቶ ለመድረስ ታስቦ እስካሁን አፈጻጽሙ 65 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል። ለጤናው ዘርፍ ግቦች አለመሳካትም የጸጥታ ችግር፣ ቅንጅታዊ አሰራር ማነስ፣ የሕብረተሰብ ተሳትፎ ማነስ፣ በቂ የህክምና መሳሪያ አለመኖር፣ የተጠያቂነት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር እንዲሁም የአመራሮች መለዋወጥ እንደ ተግዳሮት ተጠቅሰዋል። የውሃ ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሸዋነሽ ደመቀ እንዳሉትም በውሃ ዘርፍ የተቀመጠው እቅድ በጣም የተለጠጠ እንደሆነ ገልጸው፤ 'አሁንም እቅዱን እንደርሳለን ብለን አናስብም' ብለዋል። "አሁን በደረስንበት ደረጃ ላይ በመመስረት  ዕቅዱን ማሳካት እንደማይቻል ነው" የሚል ግመታቸውን ያስቀመጡት። ከአምስት ዓመቱ ዕቅድ መሰረትም እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ በአራት ዓመታት ለመሳካት ከታቀደባቸው መስኮች መካከል በአዳዲስ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት 47 በመቶ፣ በከተሞች የውሃ አቅርቦት 53 በመቶ መሆኑን አንስተዋል። በተጠቃሚዎች ረገድም በገጠር ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚዎች 74 በመቶ፣ በከተሞች 73 ነጥብ 6 በመቶ፣ በብሔራዊ ደረጃ ደግሞ 73 ነጥብ 7 በመቶ ሲሆን በውሃ አቅርቦት ተደራሽነት በገጠር 78 በመቶ፣ በከተሞች 54 በመቶ፣ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ 71 በመቶ መሆኑ ተገልጿል። በትላልቆቹም ሆነ በገጠር ከተሞችም በርካታ የውሃ ጉድጓዶች የውሃ መጠን በመቀነሱ የውሃ እጥረቶች መከሰቱን ገልጸው፤ ዘላቂና ከአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የውሃ አካላትን በመፈለግና በማጥናት ስራዎችን ለማከናወን ታቅዷል ብለዋል። በውሃ ጥራት መጓደል ተጠቂ የሆኑ ከ400 በላይ ወረዳዎች እስከ 10 በመቶ ያለውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢንቨስትመንት ለመጀመርም እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ከልማት አጋሮች ተወካይ በኦስትሪያ ልማት ትብብር ተወካይ ስቴቬን ሃልቫክ እንዳሉት መንግስት በብሔራዊ ደረጃ የተሻለ ለመፈፀም ቢጥርም አሁንም ግን ረጅም ጉዞ ይጠይቃል። በዕቅዱ ስኬት አመላካች መስፈርቶች ግምገማ መሰረትም የጤና፣ የትምህርትና የውሃ ልማት መሰረታዊ አገልግሎቶች በዚህ ዓመት በሚጠናቀቀው ሳይሆን በቀጣይ ታቅደው በሚተገበሩ አገራዊ የልማት ዕቅዶች የሚፈጸሙ ናቸው ብለዋል። በዕቅዱ የታሰቡና ወደፊት ገቢራዊ የሚደረጉ ዕቅዶች ዋናው መለኪያና አካታችናነት እንዲሁም ጥራቱ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን ለማሳካት መንግስት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም