በሾኔ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ዘይት፣ ስኳር እና ቡና አከማችተዋል የተባሉ ግለሰቦች ተያዙ

106
ሆሳእና ኢዜአ ህዳር 2/2012ዓ.ም በሀድያ ዞን ሾኔ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ የምግብ ዘይት ፣ ስኳር እና ቡና አከማችተዋል የተባሉ ሶስት ግለሰቦች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ንብረቱ  የተገኘው  ትናንት  በከተማዋ  በሚኖሩ የግለሰቦቹ  ቤቶች  ውስጥ ተከማችቶ ነው፡፡ ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ በቤቶች ባደረገው  ፍተሻ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሁለት ሊትር ዘይት፣ ሰባት ኩንታል ቡና እና ሶስት ኩንታል ስኳር ማግኘታቸውን የከተማዋ አስተዳደር  ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጅን ታረቀኝ ሶረቶ ለኢዜአ ገልጸዋል። "በመንግስት ድጎማ ለህብረተሰቡ የሚቀርበውን በተለይ  ዘይት እና ስኳር አለአግባብ  አከማችቶ ማስቀመጥ ተጠያቂ ያደርጋል "ብለዋል፡፡ ፈቃድም ሆነ ሌላ ማስረጃ ሳይኖራቸው ንብረቱን በህገወጥ መንገድ በየቤታቸው አከማችተው ተገኝተዋል የተባሉ ሶስቱ ግለሰቦች ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን አስረድተዋል። ህብረተሰቡ በወንጀል ተባባሪ የሆኑ አካላትን በመጠቆምና በማጋለጥ  ለህግ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት አዛዡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም