በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ነገ መከላከያ ከባህርዳር ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ይጫወታሉ

60
ህዳር 2/2012 በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቀጣይ ጨዋታዎች ነገ መከላከያ ከባህርዳር ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከወልቂጤ ከተማ ይጫወታሉ። 14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በስምንት ክለቦች መካከል እየተደረገ ይገኛል። በዚህም በመጀመሪያው የጨዋታው መክፈቻ ቀን ባህርዳር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በባህርዳር 1 ለ 0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ በመከላከያ 2 ለ 1 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። እንዲሁም በውድድሩ ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን 1 ለ 0  ሲያሸንፍ ሰበታ ከተማ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን በተመሳሳይ 1 ለ 0 መርታቱም የሚታወስ ነው። የከተማ ዋንጫው ቀጣይ ጨዋታዎች ነገ ቀጥለው የሚውሉ ሲሆኑ ከቀኑ በ 9:00 ሰዓት መከላከያ ከባህርዳር ከተማ ጋር ይጫወታሉ። እንዲሁም ከቀኑ በ11:00 ሰዓት ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ ጋር እንደሚጫወቱ ለማወቅ ተችሏል። ከነገ በስቲያ ሐሙስ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከሰበታ ከተማ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9:00 ሰዓት እና 11:00 ሰዓት በተከታታይ ይጫወታሉ። በዋንጫው ስምንት ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፈልው እየተወዳደሩ የሚገኙ ሲሆኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና መከላከያ በምድብ አንድ ተደልድለው ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ሰበታ ከተማ ደግሞ በምድብ ሁለት የተደለደሉ ክለቦች ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት የቻለ ሲሆን፤ ኢትየጲያ ቡና ደግሞ 4 ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት ችለዋል። እንዲሁም ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ዋንጫውን ሲያነሳ ፈራሹ ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ደግሞ 1 ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል። 14ኛ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም ይፈጸማል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም