የህዳሴው የኮርቻ ግድብ የፊት ገጽ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ ተጠናቀቀ

59

ህዳር 2/2012 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኮርቻ ግድብ የፊት ገጽ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ ዛሬ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ።

የኮርቻ ግድብ የፊት ገጽ በኮንክሪት የመለበድ ሥራ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ዛሬም የመጨረሻው የፊት ገጽ ኮንክሪት ሙሌት ሥራ ተከናውኗል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ምህንድስና ሥራዎች ቁጥጥር ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ መንግስቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አጠቃላይ የኮርቻ ግድቡ የፊት ገጽ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ ከ330 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ኮንክሪት ፈጅቷል።

የፊት ገጽ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ መጠናቀቁ በሥራው ላይ የነበሩ ባለሙያዎችና ማሽኖች ወደ ዋናው ግድብ በመሄድ አጠቃላይ የዋና ግድቡን ሥራ እንዲፋጠን ያደርጋል ብለዋል።

ዋናው ግድብመያዝ ካለበት የውሃ መጠን በላይ ሆኖ ሲፈስ የሚቀረውን ውሃ በመያዝ ከግድቡ የሚፈለገውን ኃይል ለማመንጨት የኮርቻ ግድቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በኮርቻ ግድቡ ዋነኛ የሆነው የፊት ገጽ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ እንደሆነና ቀሪ የኮርቻ ግድቡ የማጠናቀቂያ የሲሺል ምህንድስና ሥራዎች በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቁ ጠቁመዋል።

የማጠናቀቂያ የሲሺል ምህንድስና ሥራዎቹ ውሃ ወደ ሌላ ቦታ እንዲፈስ የመጠበቅ ተግባር እንደሆነም አስረድተዋል።

ለኮርቻ ግድቡ የሚሆን ቦታ የመለየት፣ የመቆፈር፣ የመመንጠርና ለግንባታ ዝግጁ የማድረግ ሥራ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራው ከተጀመረበት 2004 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

የኮርቻ ግድቡ ሥራ የኢትዮጵያ ባለሙያዎችና ሠራተኞች በግድብ ግንባታ ያላቸውን የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ግንዛቤ እንዲያድግና እንዲዳብር ይደረገ ነው ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኮርቻ ግድብ 5 ነጥብ 2 ኪ.ሜ ርዝመት እና 50 ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን ለእስካሁኑ የኮርቻ ግድብ ስራ 14 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት ስራ ላይ ውሏል።

የኮርቻ ግድቡን ጨምሮ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ምህንድስና ሥራዎች በኢጣልያው የግንባታ ስራ ተቋራጭ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን የሚከናወን መሆኑ ይታወቃል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካው የሶስትዮሽ ውይይት በኋላ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አጠቃላይ የኮርቻ ግድቡ ሥራ 9 ነጥብ 5 በመቶ እንደተጠናቀቀ መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም