በኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር ለማዘመን የሚውል የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

76
ኢዜአ ህዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም የአሜሪካ አለም ዓቀፍ የልማት ድርጅት /USAID/ በኢትዮጵያ የመሬት አስተዳዳርን ለማዘመን የሚውል የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ። ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ አስራ አንድ ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደቡም ታውቋል። በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ ሲያን ጆንስ እንዳሉት ዛሬ ይፋ የሆነው ፕሮጀክት  በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የመሬት አስተዳደር ስርዓትን ለማዘመን ያለመ ነው። ፕሮጀክቱ በመሬት ዙሪያ ስልጠና ለሚሰጡ፣ ጥናት ለሚያደርጉና የፖሊሲ ሃሳቦችን ለሚያመነጩ ድጋፍ የሚያደረግና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ስርዓትን ለማሳለጥ የሚሰራ ነው። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በገጠር አርሶ አደሩ በመሬቱ የመጠቀም መብቱን ለማረጋገጥ የሚሰራውን ስራ ለማገዝ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በቀጣይም በከተማ የሚኖሩ ዜጎች በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸው በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲረጋገጥ ማድረግና ከተሞች ሲስፋፋም እንዴት ከገጠሩ ጋር ተስማምተው መስራት እንደሚችሉ አሰራሮችን የመዘርጋት ስራን ይደግፋል ብለዋል። በተጨማሪ በአርብቶ አደር አካባቢ የመሬት የመጠቀም መብታቸውን የሚያረጋግጡ ተግባራት እንዲሻሻሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። በተለይ በሶማሌ፣በአፋር፣ በጉጂና ሌሎች አርብቶ አደር አካባቢዎች  በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸውን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት እንዲያገኙ የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር የሚከናወኑ ተግባራትን ከሚመለከታቸው ጋር ይሰራል ተብሏል። በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢ በመሬት የሚነሳውን ግጭት ለመቀነስና የአርብቶ አደሩ ኑሮ እንዲሻሻል ፕሮጀክቱ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት። ፕሮጀክቱ ለቀጣይ አስራ አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን የአምስት ዓመቱ በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል ብለዋል። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ታዜር ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው የዛሬው ፕሮጀክት በገጠር የሚኖሩ አርሶ አደሮች የመሬት የመጠቀም መብታቸውን ለማረጋገጥ የሚሰራውን ስራ ለማጠናከር ነው። ፕሮጀክቱ በከተሞች የተጀመረውን የካዳስተር ምዝገባንም ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል። በኢትዮጵያ ያለውን መሬት በአግባቡ ባለመያዝ፣ ባለማስተዳደር እንዲሁም በመረጃ አያያዝ ክፍተትና በቴክኖሎጂ እጦት  ሳቢያ ግጭቶችና ክርክሮች ይነሳሉ። ይህንንና መሰል በመሬት ዙሪያ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ታዲያ ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት። በተጨማሪም የከተማ ነዋሪዎች በመሬታቸው የመጠቀምና የባለቤትነት መብታቸው ላይ እርግጠኛ እንዲሆኑ የባለቤትነት ሰርተፍኬት እንዲያገኙ ያደርጋልም ነው ያሉት። በኢትዮጵያ አርሶ አደሩ የገጠር መሬት የመጠቀም መብቱን ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ ከ15 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የባለቤትነት ሰርተፍኬት እንዳገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም