የአንበጣ መንጋ ወደሐረሪ ክልል እንዳይገባ እየተሰራ ነው

102
ሐረር (ኢዜአ) ህዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአጎራባች ክልሎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወደሐረሪ ክልል እንዳይገባ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቢሮው የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አዱኛ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በክልሉ አጎራባች አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እስከአሁን ድረስ ወደ ክልሉ አልተዛመተም፡፡ በክልሉ አቅራቢያ በሚገኙ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች፣ በድሬዳዋና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወደክልሉ ገብቶ በእጽዋትና በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ለእዚህም ባለሙያዎችን ያቀፈ ግብረ ኃይል ተቋቋሞ የክትትልና አርሶ አደሩን የማነቃነቅ ሥራ በመሰራት ላይ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል። "አርሶ አደሩ የአንበጣ መንጋውን በባህላዊ መንገድ መከላከል እንዲችል የሚያግዙ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው" ሲሉም ገልጸዋል። የአንበጣ መንጋው ቢከሰት አርሶ አደሩን እንዴት ማገዝ እንደሚቻል ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች መሰራታቸውንም አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡ በቅድመ መከላከል ሥራው ከባለሙያና ከቁሳቁስ በተጨማሪ 200 ሊትር ኬሚካል መዘጋጀቱን ነው ያመለከቱት። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የደረሰ ሰብል መኖሩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ "ሰብሉ በአንበጣ ጉዳት እንዳይደርስበት ቀደም ብሎ የመሰብሰብ ሥራ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ፣ በአጎራባች ክልሎችና በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ርብርብ ቢሮው በባለሙያ፣ በቁሳቁስና በተሽከርካሪ ድጋፍ እየደረገ ነው። የአንበጣ መንጋ በክልሉ ከ11 ዓመት በፊት ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ በቢሮው የምርምር፣ ስርፀት እና አርሶ አደር ግንኙነት ባለሙያ አቶ ባህር አብዱላሂ ናቸው፡፡ በአሁኑ ውቅት በክልሉ አጎራባች አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በክልሉ ቢከሰት ፈጥኖ መቆጣጠር እንዲቻል ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ ከአርሶ አደሩ ጋር  እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ለዚህም እስከቀበሌ ድረስ በመውረድ የአርሶ አደሩን ስነ ልቦና ከማዘጋጀት ባለፈ በባህላዊ መንገድ መቆጣጠርና መከላከል እንዲችል የማነቃቃት ሥራ እየሰራን እንገኛለን’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አጎራባች አካባቢዎች የክልሉ ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም