መሰረታዊ የጤና አገልግሎት መርሃ ግብር ማሻሻያ ይፋ ሆነ

49
ህዳር 2/2012 ጤና ሚኒስቴር መሰረታዊ የጤና አገልግሎት መርሃ ግብርን (ፓኬጅ) ማሻሻያን ዛሬ ይፋ አድርጓል። የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን መርሃ ግብሩን(ፓኬጁን) ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት አሁን ካለው የህዝብ ፍላጎት ጋር አብረው የሚሄዱ አሰራሮችን መተግበር አስፈላጊ በመሆኑ ማሻሻያው መደረጉን ተናግረዋል። የተሻሻለው የጤና አገልግሎት መርሃ ግብር እስከ አስር ዓመት የሚያገለግል ሲሆን ቀደም ሲል የነበረውን የጤና የአገልግሎት መርሃ ግብርን ክፍተት የሚሞላ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ''ማሻሻያው በጤና ተቋሟት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችን ምንነት ከመለየት ባሻገር፤ ለየትኛው ታካሚ ምን ዓይነት አገልግሎት ይሰጣል? የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል መፍትሔዎቹ ምንድን ናቸው? የሚሉትንም ለይቶ የሚያስቀመጥ ነው'' ብለዋል። የመጀመሪያው መርሃ ግብር ከ12 ዓመታት በፊት የተዘጋጀ ሲሆን አገልግሎቱም በ184 የአገልግሎቶች ዘርፎች ብቻ የተወሰነ እንደነበር ገልጸዋል። አዲስ የተሻሻለው የጤና መርሃ ግብር ቀደም ሲል የነበረውን ጉድለት የሚያስተካክልና 1ሺህ 84 አገልግሎቶችን በማካተት የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል። ከተጨመሩት የጤና አገልግሎቶች መካከል ቀደም ሲል ይሰጥ ከነበረው ለሦስት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የህክምና  አገልግሎቶች ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ማድረግ መቻሉንም እንዲሁ ለአብነት አንስተዋል። መርሃ ግብሩም በሁሉም ጤና አገልግሎት ተቋማት ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ በሁለተኛና በሦስተኛ ደረጃ በመንግስትና በግል የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግም የሚያግዝ መመሪያ ነው ብለዋል። አገሪቷ በጤናው ዘርፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት እ.አ.አ እስከ 2030 ድረስ የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ትኩረት ሰጥታ በእቅድ እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የዜጎች በዓመት የጤና አገልግሎት (የነፍስ ወከፍ) ዝቅተኛ ወጪ 32 ዶላር መድረሱን ገልጸው በዚሁ አግባብ እ.አ.አ በ2030 በተያዘው እቅድ እያንዳንዱ ኢትዮጵያውያን ዜጋ ከፍ በማድረግ የጤና ወጪ ወደ 44 ዶላር ለማድረስ እንደሚቻል ተናግረዋል። የጤና ማሻሻያው መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ያሉት ዶክተር አሚር፤ የጤና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑም ታምኖበታል። በተጨማሪም ማሻሻያው የጤና አገልግሎቱ ጥራትን፣ ፍትሐዊነትንና ግልጸኝነትን ለማስፈን፣ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም ባገናዘበና በተሻለ አፈጻጸም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል። በመሆኑም ይህንን መርሃ ግብር ለማሳካት በየጤና ተቋሟቱ መሰረተ ልማት ማሟላትና የባለሙያዎች  ስልጠና የመስጠት ስራ በትኩረት ይከናወናልም ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም