በሶማሊያ ጠንካራ ስርዓት የመመስረት ስራውን ለማገዝ ከኢትዮጵያ ልምድ እንጋራለን - አፈ ጉባኤ ሞሐመድ ሙርሳል

70

ህዳር 2/2012 "በሶማሊያ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመመስረት ስራውን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት ማጎልበት እንፈልጋለን" አሉ የሶማሊያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሞሐመድ ሙርሳል።

በሶማሊያ ፓርላማ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሞሐመድ ሙርሳል የሚመራ ልኡክ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ አቻቸው ከአፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ሊያጠናክሩ የሚችሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን በተለይም በፓርላማው መካከል ቋሚ ግንኙነት መመስረት እንደሚገባ ተማምነዋል።

በግንኙነቱ ሂደትም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ በርካታ ልምዶች መውሰድ እንደምትፈልግና በተለይም አሁን በሶማሊያ የተጀመሩ የዴሞክራሲ፣ ሰላምና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያን አጋርነት የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጥ ላይ በመሆኗ ሶማሊያ ከዚህ መማር ትችላለች ብለዋል።

በተለይም ከፓርላማ ጀምሮ መንግስት 50 በመቶ የሚሆኑ ካቢኔዎቹን ሴቶች ማድረጉ የሴቶችን አመራርነት ከፍ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

አዲስ የምርጫ ህግ መውጣቱም ሶማሊያ ቀጣይ ለምታደርገው ምርጫ ትልቅ ተሞክሮ ሊሆናት እንደሚችልና በማንኛውም ጉዳይ ላይ ልምድ ለማካፈል ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱንም ለማጠናከር ሁለቱ ፓርላማዎች የጋራ መደበኛ ግንኙነት የሚመሰርቱበት ኮሚቴ ማቋቋም እንደሚቻልም ተስማምተዋል።

ከኢትዮጵያ የፓርላማ አባላት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ በሶማሊያ ደግሞ ሴቶች 20 በመቶውን ይሸፍናሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም