የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መረጃን ወደ አንድ ቋት ለማሰባሰብ የሚያስችል አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

87
ህዳር 2/2012 በአገሪቷ እየተስተዋለ የመጣውን የስራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስና ህገ ወጥ ደላሎችን ሊያስቀር የሚችል የስራ ዕድል ፈጠራ መተግበሪያ ስልት በቅርቡ ሊጀመር መሆኑን የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታወቀ። አገሪቷ የምታመነጨው ኢኮኖሚና የውልደት መጠን አለመመጣጠን በስራ ፈላጊውና በሚፈጠረው ስራ መካከል መዛባትን አስከትሏል። ከዚህም በላይ የመንግስት አሰራር በአግባቡ እንዳይተገበርና በአቋራጭ ለመክበር የሚሰራው ደላላ በሁሉም መስክ መብዛት አንድ ላይ ተደምሮ የአገሪቷ የስራ አጥ ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጓል። ይኸንን መዛባት ለማስተካከልና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር እንዲያስችል ታስቦ በቅርቡ የተቋቋመው  የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በኮሚሽኑ የስርዓተ ስርጸት ዳይሪክተር አቶ ዮሴፍ ሰርጸ እንደሚገልጹት ኮሚሽኑ ስራ ፈላጊ ዜጎች ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ሳያባክኑ በቀላሉ ካሉበት ቦታ ሆነው በስራ ፈላጊነት እንዲመዘገቡ ለማድረግ የሚያስችለውን መተግበሪያ ይፋ አድርጓል። አዲሱ የመረጃ ቋት ካሁን በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ህገወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነትን በማስቀረት ህጋዊ የሆኑ ደላሎችንና የግል ድርጅቶችን ብቻ የሚያሳትፍ መሆኑን ጭምር ገልጸዋል። መተግበሪያው የስራ ፈላጊዎችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ፤ የስራ ገበያ የመረጃ ማሰባሰቢያ ቅፆች ወጥና ተናባቢ ማድረግና ከክልሎች የሚመጡ የስራ ገበያ መረጃዎች ጥራቱንና ወቅቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል እንደሚረዳም ገልጸዋል አቶ ዮሴፍ። በእለቱም የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የስራ ገበያ መረጃ በቀላሉ ወደ አንድ ቋት የማሰባሰብ ስርአት ለማዘመን እንዲያመችና በዲጅታል መሳሪያዎች የታገዘ እንዲሆን ለመዲናዋ መቶ ሃያአንድ ወረዳዎች ታብሌቶችን ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም