በዞኑ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ያለሙ አርሶ አደሮች ከእንስሳት ሀብታቸው ተጠቃሚ እየሆኑ ነው

127
ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ህዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ዞን የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ያለሙ አርሶ አደሮች ከእንስሳት ሀብት ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናገሩ። በዞኑ ደብረ ኤሊያስ ወረዳ ጫጎ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ገድፍ ይታይህ ለኢዜአ እንዳሉት ከእርሻ ስራቸው ጎን ለጎን የተሻሻለ የእንስሳት መኖ በማልማት እንስሶቻቸውን በተሻለ መመገብ ችለዋል። ከዚህ ቀደም ብዙ የአበሻ ከብቶች ቢኖራቸውም በዝርያቸውና በምግብ እጥረት ምክንያት የሚያገኙት ጥቅም አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። አርሶ አደሯ እንዳሉት የእንስሳት መኖ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መጥተዋል። በአሁኑ ወቅትም በሩብ ሄክታር ማሳ ላይ "ሮደስ" የተባለውን የተሻሻለ ሣር በማልማት ለዓመት የሚሆናቸውን የእንስሳት ቀለብ በማከማቸት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። "ባለፈው ዓመት ያደለብኳቸውን ሁለት ከብቶች በመሸጥ 40 ሺህ ብር ገቢ አግቺያለሁ" ያሉት አርሶ አደር ገድፍ፣ በአሁኑ ወቅትም ሁለት በሬዎችን አስረው ያለሙትን መኖ እየቀለቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።በማቻከል ወረዳ የእምቡሊ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አላምረው ይሁን በበኩላቸው እንዳሉት ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ  "ቤንሽ" እና "ሴታሪያ" የተባሉ የተሻሻሉ የመኖ ሣር እያለሙ ይገኛሉ። ቀደም ሲል ካሏቸው ሦስት ላሞች ከእያንዳንዱ በቀን አንድ ሊትር የማይሞላ ወተት ያገኙ እንደነበር አስታውሰው በቂ የእንስሳት መኖ መመገብ ከጀመሩ በኋላ የሚያገኙትን ወተት ከሁለት ሊትር በላይ ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል።ከእዚህ በተጨማሪ ዝርያቸው የተሻሸሉ የወተት ላሞችን በመግዛት ከአንድ ላም በቀን እስከ 11 ሊትር ወተት በማግኘት ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ነው የገለጹት። የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ መልካምናት እምሩ በበኩላቸው በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ማዳበሪያ ተጠቅመው "ሮደስ" የተባለ የሣር ዘር ካለፈው ዓመት ጀምሮ በማልማት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በተመጣጠኝ ዋጋ ገዝተው ካደለቧቸው አራት ከብቶች ከ70 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ መልካምናት በአሁኑ ወቅትም የመኖ ልማትና የማድለብ ስራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። የምስራቅ ጎጃም ዞን እንስሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት የመኖ ልማት እና ስነአመጋገብ ባለሙያ አቶ ስመኘው አዳነ በዞኑ የእንስሳትን ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። "አርሶ አደሩ ከተለያዩ የሰብል ተረፈ ምርቶች ከሚሰበስበው የእንስሳት መኖ በተጨማሪ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዘሮችን በማቅረብ በግለሰብ ማሳ እና በወል መሬቶች ላይ እንዲያለማ እየተረደገ ነው" ብለዋል። ባለሙያው እንዳሉት የመኖ ዘር ልማት በመካሄዱ ከሦስት ዓመት ወዲህ ከአበሻ እና የተሻሻለ ዝርያ ካላቸው ላሞች ይገኝ ከነበረው የወተት ምርታማነት በአማካኝ ከሁለትና ከስድስት ሊትር በላይ ጭማሬ ታይቷል ብለዋል። በእንስሳት ማድለብ ሥራ የተሰማሩ አርሶ አደሮችም በአንድ የደለበ ከብት ከ107 ኪሎ ግራም ባላይ ጭማሬ እያገኙ መሆናቸውን ነው የገለጹት። በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን መኖ ለመሰብሰብ ታቅዶ በሩብ ዓመቱ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን በላይ መኖ ከተሻሻለ የመኖ ዘርና ከሰብል ተረፈ ምርት ለመሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል። የመኖ ልማቱ መስፋፋት በዞኑ የሚገኙ ከ5 ሚሊዮን በላይ የዳልጋ እና የጋማ ከብቶችን በአግባቡ መመገብ እንዳስቻለ ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም