አፍሪካዊያን ህገ-ወጥ ስደትን ለማስቀረት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ...ምሁራን

96
ህዳር  1/2012 አፍሪካዊያን በብልሹ አሰራር፣በሙስናና በግጭቶች ምክንያት በስደት የሚያጡትን ወጣት አምራች ኃይል ለመታደግ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ። የመቀሌና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ከኔዘርላንዱ ቲልዩብ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ስደትን መከላከል ፣የወጣቶች ሰራ እድል ለማስፋፈትና የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታት ያለመ የምክክር መድረክ በአክሱም ከተማ ተካሒዷል። በመድረኩ ላይም በፓን አፍሪካ ምክር ቤት የአለም አቀፍ ግንኙነትና ግጭት አፈታት ትብብር ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሚስተር አቦበከር ሲድኪ ኮኔ "የአፍሪካ ግንኙነትና የግጭት አፈታት" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳመለከቱት አፍሪካውያን ሰላምን በማረጋገጥ ዜጎቻቸውን ከስደት መታደግ ይጠበቅባቸዋል ። የፓን አፍሪካ ምክር ቤት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ለወጣቶች የስራ እድል ምቹ ሁኔታ ለመፈጠር በትኩረት መስራት መጀመሩን ገልጸው ሃገራቱ ስደትን ለማቆም በጋራ ሊያሰራ የሚችል ፖሊሲና ህግ ሊኖራቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል። "ብልሹ አሰራር፣ሙስና እና ስራ አጥነት እንዲሁም ግጭት ዋና የስደት መንስኤ እየሆነ ነው" ያሉት ሊቀመንበሩ ችግሩን ለማስቀረት ከፍተኛ ትግል ማድረግን እንደሚጠይቅም አመልክተዋል። የዚህ ዓይነቱን መድረክ አፍሪካውያን የፖለቲካ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በምርምርና በጥናት የተደገፈ ስራ ለማከናወን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ናቸው። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋራ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው "ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከርና ሰላምና መረጋጋትን እውን በማድረግ ለወጣቶች ሰራ እድል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል" ብለዋል። የኡጋንዳ የስራ እድል አመቻች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚስ ዛሚናህ ማሎሌ በበኩላቸው 16 በመቶ የአፍሪካ ህዝብ በግጭትና ስራ አጥነት ምክንያት ኑሮውን በስደት እንዳደረገ ገልጸዋል። አፍረካ ላሉባት ችግሮች መፍትሄ ማምጣት የሚችሉ ተቋማት እንደሚያስፈልጓት በመገንዘብ መሪዎቿ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸው ''አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ያለንን የሰውና የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ ተጠቅመን አህጉራችንን ማበልጸግ እንችላለን'' ብለዋል። የዚምባብዌ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ሃላፊ ዶከተር አንድሪው ቺንዳንያ በበኩላቸው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለአህጉሪቷ እድገት በጋራ መስራት እንደሚያዋጣቸው ገልጸው ከሶስት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጀመሯቸው የምርምር ስራዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። ምሁራን በመልካም አስተዳደር፣ በሰራ እድል ፈጠራ እና ውጤታማ ፖሊሲ በማመንጨት ላይ መንግስታቱን ሊደግፉ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በምክትል ርዕሰ መስተዳደር መአረግ የትግራይ ክልል ከተማ ልማት ንግድና ኢንዱስቱሪ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ እንዳሉት መድረኩ የአፍሪካን ህዳሴ እውን ለማድረግ ምሁራን የላቀ ሚና እንዳለቸውና ተባብረው ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸው ያሳየ ነው። "በተለይ በአፍሪካ እየተባባሰ የመጣው ህገ-ወጥ ስደት ለአህጉሩ ዋነኛ ችግርና አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው" ያሉት ኃላፊው የመንግስታቱ ተባብረሮ መስራት በስደት ምክንያት የሚጠፋውን አምራቹን ወጣት ኃይል መታደግ እንደሚያስችል አስረድተዋል። ትላንት ማምሻውን በተጠናቀቀው መድረክ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንና የመንግስታት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም