የኢትዮጵያ ባዮስፌር ሪዘርቮችን ዘለቄታዊ ጥበቃና አጠቃቀምን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ይሻል

80
አዲስ  አበባ  ህዳር  1/2012 የኢትዮጵያ ባዮስፌር ሪዘርቮችን ዘለቄታዊ ጥበቃና አጠቃቀምን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ይሻል:: የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር በመሆን የሳይንስ ሳምንትን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ባዮስፌር ሪዘርቮች ዙሪያ መክሯል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በአብዛኛው የተፈጥሮ ሃብት ላይ ጥገኛ የሆኑ አገሮች የብዝሃ ህይወት ሀብታቸውን መጠበቅ ግድ ይላል። በመሆኑም የባዮስፌር ሪዘርቮች ዘለቄታዊ ጥበቃና አጠቃቀምን ለማረጋገጥ ጉዳዩ በአንድ ተቋም ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል። የከፋ ደን፣ የያዮ ቡና፣ የመጀንግ ደን፣ የሸካ ደንና የጣና ኃይቅ ኢትዮጵያ ካሏት የባዮስፌር ሪዘርቮች መካከል ለአብነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ እነዚህም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት የተመዘገቡ ናቸው። የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የምርምር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ኮሚሸነሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ናቸው፡፡ የባዮስፌር ሪዘርቮችን ለመጠቀም ሳይንሳዊ ምርምሮችን ማካሄድና የክትትል ስርዓትን በመዘርጋት በአካባቢው ለሚገኙ ማህበረሰቦች ዘላቂ ልማት ማረጋገጥንም አላማ አድርጎ እንደሚሰራም ተናግረዋል። በመሆኑም በዘርፉ ውጤታማ ለመሆንና የባዮስፌር ሪዘርቮችን ለመጠቀም የብሔራዊ የሰውና የባዮስፌር ሪዘርቭ ኮሚቴ ስራን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አክለዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፣ በአምስቱ የባዮስፌር ሪዘርቮች ውስጥ ያሉት እጽዋትና የእንስሳት ሃብቶች በርካታ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቁመዋል። የባዮስፌር ሪዘርቭ የብሄራዊ ኮሚቴው ስራ ከዘላቂ የልማት ግቦች ፣ ከአፍሪካ 2063 የልማት አጀንዳዎችና ከየሴክተሩ የትኩረት አቅጣጫ ጋር በመስራት የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባም አንስተዋል። በ2010 ዓ.ም የሰውና የባዮስፌር ሪዘርቭ ብሄራዊ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ዓላማውም በኢትዮጵያ ያለውን የባዮስፌር ሪዘርቭ ከአፍሪካ አገር ካሉት ጋር ትስስር በመፍጠር ልምዶችን ለመለዋወጥ እንደሆነም ተገልጿል። በመሆኑም ኮሚቴው በነበሩት የአደረጃጀት ለውጦች ስራውን ያቆመ ሲሆን አሁን ላይ ስራውን እንዲጀምርና በዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስመዝገብም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የባዮስፌር ሪዘርቭ እንደ አገር በቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር የነበረ ሲሆን አሁን ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም