ወጣቶችን ከግጭት ወደ ልማት ለማምጣት ስለሰላም ማሳወቅና በስራ ማሰማራት ይገባል

64
(ኢዜአ)   ህዳር ቀን 2012 ወጣቶች በትግል ወቅት ሲጠቀሙበት የነበረውን ስልት በመተው በልማት ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ከታጠቁት ሃሳብ በማስፈታት ስለሰላምና ልማት ማሳወቅና ወደስራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ። በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ሀገራት የስርዓተ ፆታና ሰላም ጉዳዮች ተመራማሪና አማካሪ ዶክተር መሰረት ካሳሁን እንዳሉት ከኢትዮጵያ ህዝብ 70 በመቶ ያህሉ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች የዛሬ ሀገር ሰሪና የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸውም በሀገር ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ በሀገሪቷ ለመጣው ለውጥ ወጣቱ ጉልህ ድርሻ እንደነበረውም ተናግረዋል። ወጣቶቹ ለውጡ በመጣ ማግስት ማግኘት ያለባቸውን የስራ እድልና መሰል ነገር ባያገኙም የትግል ስልታቸውን ግን መለወጥ እንዳለቻበው ነው ያስረዱት ዶክተር መሰረት። ወጣቶች የፈለጉት ለውጥ ከመጣና ድል ካገኙ በኃላም ቢሆን በመስኩ የተሰራው አመርቂ ስራ ባለመኖሩ  "በፊት ሲጠቀሙበት የነበረውን የትግል ስልት አሁንም እየተጠቀሙ ነው" ያሉት ዶክተር መሰረት፤ ወጣቱን ለትግል ያነሳሱ አካላት ለሰላምና ልማትም ማነሳሳት እንዳለባቸውም አስረድተዋል። ወጣቶች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መዳረጋቸው ግባቸው ላልተለዩ ቅስቀሳዎች ሁሉ ዝግጁ እንደሚያደርጋቸው ገልፀው፤ ወጣቶች ለመሰል ችግር መዳረጋቸው ተስፋ እንዲቆርጡ በማድረግ ለአሸባሪ ድርጅቶች ጭምር እንዲሰሩ እንደሚያደርጋቸውም አንስተዋል። ወጣቶች አሁንም ወደ ግጭት ማምራት እንደሌለባቸው ገልፀው ወጣቶቹ ከግጭት ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማድረግ የማህበራዊና ስነልቦናዊ ተሃድሶ እንዲሁም የአብሮነት እሳቤ ጋር ማያያዝ ይገባልም ነው ያሉት። በቅርቡ 10 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የስራ እድል እየተመቻቸ መሆኑ እነዚህን ወጣቶች በስራ በማሰማራት ለኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል። ወጣቶቹ ለሰላምና ልማት አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ከቀድሞ የትግል ስልት መውጣት እንዳለባቸውና በስራ ተሰማርተው ሀገርን እንዲያለሙም የመንግስት፣ የምሁራንና የሁሉም ኀብረተሰብ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በምስራቅ አፍሪካ ያለው የሰላም እጦትና መሰል ቀውስ ወደ ኢትዮያ እንዳይመጣ የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም