ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ በዓለም የዩኒቨርስቲዎች እግር ኳስ ውድድር ይካፈላል

112
ኢዜአ ህዳር 1 ቀን 2012ዓ.ም ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ በቻይና በሚካሄደው የዓለም የዩኒቨርስቲዎች እግር ኳስ ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ ይጫዎታል። የኢትዮጵያው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ውድደር የተጋበዘው ባለፈው ዓመት መቀሌ በተካሄደው የመላ አፍሪካ የዩኒቨርስቲዎች ውድድር በእግር ኳስ አሸናፊ በመሆኑ ነው። የዓለም ዩኒቨርስቲዎች እግር ኳስ ዋንጫ በቻይናዋ ጅንጅያንግ ከተማ ከህዳር 11 እስከ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። በዚህ ውድድር በእግር ኳስ ከአምስቱ አህጉር የተውጣጡ በወንዶች 16 ቡድኖች በሴቶች ስምንት ቡድኖች ይካፈላሉ። ዩኒቨርስቲው ለዚህ ውድድርም ከባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ አሰልጣኙና ተጫዎቾች ተናገረዋል። በውድድሩም ጥሩ ውጤት ለማስመዘገብ የሚያችስል ቅድመ ዝግጀት እያደረጉ እንደሆነ ተጫዎቾች ተናገረዋል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዩኒቨርሲቲው ተጫዋቾች ይርጋ ንጉሴ ና ተመስገን ዓለማየሁ  እንዳሉት በውድድሩ ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ተዘጋጅተዋል። ወደ ስፍራው የሚያቀኑትም የተሻለ የቡድን መንፈስና የተፎካካሪነት አቅም ሰንቀው መሆኑን ተናግረዋል። የቡድኑ አሰልጣኝ ዶክተር ወገኔ ዋልተንጉስ፤ በውድድሩ ጥሩ ነገር ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅቶች ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በውድድሩ ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ትምህርት ቤቶች የስፖርተኞች መፍለቂያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማሳየትም ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል። የዩኒቨርስቲዎች የዓለም ዋንጫ ብዙ እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በእግር ኳስ ሲካሄድ ግን ይህ የመጀመሪያው ነው። በዚህ መድርክ ኢትዮጵያ አንዱ አካል መሆኗ ትልቅ እድል መሆኑን አሰልጣኙ ተናገረዋል። ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ በምድብ ሁለት ከታይላንዱ ባንኮክ ቶንቦሬ ዩኒቨርስቲ፣ ከሜክስኮው አውቶኖሞስ ዩኒቨርስቲ እና ከቻይናው ቤጂንግ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር ተደልድሏል። የልዑካን ቡድኑ አባላት በመጪው ሰኞ ለውድድሩ ወደ ቻይና የሚያቀኑ ይሆናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም