የኦሮሚያ ክልል በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተቀሰቀሰ ብጥብጥ ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች የተሰማውን ሃዘን ገለጸ

116
ኢዜአ፤ ቅምት 30/2012 የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተቀሰቀሰ ብጥብጥ ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች የተሰማውን ሃዘን ገለጸ። ''በፖለቲካ ቁማር የሰከሩ ፓርቲዎች የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ አንጀንዳዎችን እየቀረጹ ሰላም እና ጸጥታ በማወክ ህዝብን ውዥንብር ውስጥ እየከተቱ ነው'' ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በብጥብጡ ህይወታቸውን ባጡ ተማሪዎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጾ፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ "በተለያዩ ጊዜ ለህዝብ እንደምንገልጸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ በህዝቦች ላይ የራሳቸውን አጀንዳ በግድ እየጫኑ ነው" ብለዋል። አቅጣጫዎችን በመቀያየር በህዝቦች መካከል ግጭትና መቃቃር በመፍጠር ልዩነት እንዲሰፋ ለማድረግ እንደሚጥሩ አመልክተው፤ በፖለቲካ ንግድ የሰከሩ ኃይሎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በፈጠሩት አጀንዳ ኢትዮጵያውያን አላስፈላጊ የሆነ መስዕዋትነት እየከፈሉ እንደሆነ ገልጸዋል። ''በፖለቲካ ንድግ የሰከሩ ፓርቲዎች የህዝቡን ለሳለም ለማደፍረስ የተለያዩ አጀንዳዎችን እየቀረጹ አገሪቷን ሰላም ለመንሳትና ህዝብን ውዥንብር ውስጥ ለመክተት እየሰሩ ይገኛሉ'' ብለዋል። በማንኛውም መመዘኛ በተወሰኑ የፖለቲካ ቁማርተኞች የተፈጸመው ድርጊት ተቀባይነት እንደሌለው በአጽንኦት ጠቁመው፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አምርሮ የሚቃወም መሆኑን ገልጸዋል። የክልሉ መንግስት ድርጊቱን የፈጸሙትን አካላት ከፌዴራል እና ከአማራ ክልላዊ መንግስት ጋር በመሆን ለህግ ቀርበው የእጃቸውን እንዲያገኙ ጠንክሮ እንደሚሰራም አመልክተዋል። በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚሰሩ ሃይሎች አጀንዳዎችን በመቅረጽ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሰላምን በማደፍረስ መንግስትን ለማዳከምና ትዕግስት በመሳጣት ተስፋ የማስቆረጥ ተግባር በመፈጸም ወደ አላስፈጊ እርምጃ እንዲወሰድ እያሴሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ''በአቋራጭ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ በፍጹም የማይታሰብና የማይሆን ነገር ነው'' ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ''የተለያዩ አካላት ውስጥ በመደበቅ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም በአገራችን ህዝቦች የጋራ ጥቅም በተጻራራ የሚደረገው ድብቅ ዓለማ እንይዳሳካ አምርረን እንታገላለን'' ብለዋል። ህዝቡም የሚፈጽሙትን ሴራ ላይ በመንቃት እንዲጠነቀቅና የፖለቲካውን ሴራ ለማክሸፍ በአንድነት እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውን ከኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በሌላ በኩል የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሀብታሙ ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ብጥብጥ የተከሰተው ተማሪዎች ትናንት ምሽት ኳስ አይተው በተመለሱበት ወቅት ነው። በብጥብጡ የሁለት ተማሪዎች ህይወት ሲያልፍ በስምንት ተማሪዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። የብጥብጡን መንስኤ ለማወቅና አጥፊዎችን በሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ የማጣራት ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ኮማንደር ሀብታሙ አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ሰላም ወደነበረበት ተመልሷል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም