አገር ዓቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ረቂቅ ፖሊሲ ተጨማሪ አስተያየት እንዲካተትበት ወደ ቀጣይ ዓመት ተሸጋገረ

108
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 በያዝነው ዓመት ጸድቆ ይተገበራል የተባለው አገር ዓቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ረቂቅ ፖሊሲ ተጨማሪ አስተያየት እንዲካተትበት በሚል ወደሚቀጥለው ዓመት መሸጋገሩን የወጣቶችና ስፖርት  ሚኒስቴር አስታወቀ። በኢትዮጵያ በክረምት ወቅት በተለያዩ የሙያ መስኮች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች ቁጥር በየዓመቱ እያደገ መጥቷል። በዚህም ሚኒስቴሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያስገኘ ያለው ውጤት እየጨመረ በመምጣቱ ተግባሩን በፖሊሲ ለመደገፍ ባሳለፍነው ዓመት ረቂቅ ፖሊሲ እያዘጋጀ መሆኑንና በያዝነው ዓመት ረቂቁ በሚመለከተው አካል ጸድቆ ተግባራዊ እንደሚሆን መግለጹ ይታወሳል። በሚኒስቴሩ የወጣቶች ማካተት፣ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ማትያስ አሰፋ እንዳሉት ቀድሞ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት የተጠናቀቀ ቢሆንም ፖሊሲው አጠቃላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ባካተተ መልኩ ቢዘጋጅ የሚል አስተያየት መምጣቱን ገልጸዋል። በዚህም ሚኒስቴሩ አስተያየቱን በመቀበል ረቂቅ ፖሊሲው ከወጣቶች በጎ ፈቃድ ፖሊሲ 'የዜጎች በጎ ፈቃድ ፖሊሲ' ወደሚል ስያሜነት ተቀይሯል ብለዋል። ፖሊሲው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ እንዲሆን ለማስቻል በአዲስ መልክ በመቅረጽ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከህግ እይታ አንጻር አስተያየት እንዲጨምርበት መደረጉን ገልጸዋል። የረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ በ2011 በጀት ዓመት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል። "ፖሊሲው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስትና የግል ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ዕድል ይፈጥራል" ያሉት አቶ ማትያስ የበጎ ፈቃደኞችን ቁጥር ለማሳደግና ዜጎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያደርጋልም ብለዋል። ከዚህ ባለፈ ፖሊሲው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ዜጎች በስራ ላይ ለሚያጋጥማቸው አደጋ ከለላ የሚያገኙበትና የሚደገፉበትን መንገድ አካቷል።  የፖሊሲው ዝግጅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሻለ ልምድ ካላቸው አገራት መካከል  የደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ፣ ካናዳና ሩዋንዳ ልምዶችን እንደ መነሻ ተወስደዋል። በመሆኑም ፖሊሲው ከተዘጋጀ በኋላ በበጎ ፈቃደኝነት  አገልግሎት ለሚሰጡ ዜጎች ለሰጡት አገልግሎት እውቅና በመስጠት እንደ ስራ ልምድ ሆኖ እንደሚያገለግላቸው ተደርጎ በፖሊሲው መካተቱን አቶ ማትያስ አክለዋል። ባለፈው አመት በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በገንዘብ ሲተመን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎች ያለክፍያ መከናወናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም