የህጻናት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር አለበት-ሚኒስቴሩ

41
ኢዜአ ጥቅምት 29/2012፡- የህጻናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት የሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አመለከተ፡፡ " መጪዉ ዘመናችንን በዛሬዎቹ ህጻናት እንመልከት" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የህጻናት ቀንን  በሆሳዕና ከተማ  ተከብሯል፡፡ በሚኒስቴሩ የህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት እንዳሉት መስሪያ ቤታቸው  በሀገርና አለም አቀፍ ደረጃ የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የተለያዩ ስምምነቶችንና የማስፈጸሚያ ሰነዶችን በመፈራረም ዘርፈ ብዙ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ በሀገሪቱ የህጻናትን መብትእና ደህንነት እንዲጠበቅ  በሀገሪቱ ህገ መንግስት እንዲካተት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ከባለድርሻ አካላትጋር በመሆን ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ህጻናት የሚበዙባቸውን ክልሎች በጥናት በመለየት ለድጋፍና እንክብካቤ ስራ ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋልል፡፡ በሰራውም መሻሻል  መምጣቱን የገለጹት ሚኒስተር ዴኤታዋ በህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ከጎዳና ህይወት ወጥተው ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ ህጻናት ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እና በመንግስት ተቋማት ሰራተኞች የሚደረገው  ድጋፍ የህጻናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ የደቡብ ህዝቦች ክልል ሴቶች ፣ህጻናትእና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው በበኩላቸው  በክልሉ  የጎዳና ተዳዳሪነት ጨምሮ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን ለመታደግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። "በክልሉ ባሉ የሴቶች ልማት ቡድኖችና አደረጃጀቶችን በመጠቀም ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ ለችግር ተጋላጭ ህጻናትን ወደ ጎዳና እንዳይወጡ እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ እየተደረገ ነው " ሲሉ ጥረታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ በርካታ ህጻናት ለጎዳና ህይወት የሚዳረጉባቸዉን አካባቢዎች ከሀዋሳ ዩንቨርስቲ ጋር በመሆን ጥናት ተደርጎ መለየቱን አመልክተዋል፡፡ ህጻናቱን ወደ አካባቢያቸው በመመለስ መማር እንዲችሉ በማድረግ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡ በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን አመራሮች እንዲሁም ህጻናትና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም