የኃይል አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፈታት ይገባል--- አቶ ርስቱ ይርዳው

71
ሀዋሳ ኢዜአ ጥቅምት 29 ቀን 2012፡ - ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አሳሰቡ። በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እና መፍትሄው ዙሪያ የመከረ ሰባተኛ ዙር የጋራ ፎረም በሀዋሳ ተካሂዷል። አቶ ርስቱ በወቅቱ እንዳሉት ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በህብረተሰቡ፣ ባሀብቶችና በአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት በኩል የሚነሱ በርካታ ችግሮች አሉ። ችግሮቹን ለመፍታት በክልሉ መንግስት፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎት ተቋማት የጋራ ፎረም ተቋቁሙ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰዋል። ፎረሙ በስድስት ዙሮች ባካሄዳቸው የጋራ ውይይት በህብረተሰቡ ይነሱ የነበሩ ፍላጎቶችና ችግሮችን ማቃለል ቢቻልም ከአቅርቦት ስርጭትና ፍላጎት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች አሁንም መኖራቸውን ጠቁመዋል ። ፎረሙን በማጠናከር ችግሮቹን  በጋራ ለመፍታት መትጋት እንደሚገባ አመላክተዋል። ባለፈው ዓመት በክልሉ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር በዘመኑ የታቀዱ ስራዎችን በበቂ ደረጃ ማከናወን ባለመቻሉ ተጨማሪ ውዝፍ ስራ እንደሆነ ጠቁመዋል። "በተያዘው የበጀት ዓመት ያመለጡ እድሎችን መጠቀም ይቻል ዘንድ የማካካስ ስራ የሚከናወንበት መሆን አለበት" ብለዋል። የኤሌክትሪክ ኃይል በስርጭትንም ሆነ አገልግሎት አሰጣጡን ፍትሀዊ በማድረግ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ  አቶ ርስቱ አሳስበዋል ። የደቡብ ክልል ውሀ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው በኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭት ክፍተት በክልሉ በርካታ ከተሞችና መንደሮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ  ተናግረዋል ። በክልሉ የሚገኙ ኢንደስትሪዎች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻዎች፣ የጤና፣ የውሀና የመስኖ ተቋማት ግንባታዎች ተጠናቀው በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት ችግሩን ለመፍታት  በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሀም በላይ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎትና አቅርቦት ለማመጣጠን የታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል ። የሚመነጨውን ኃይል በፍትሀዊነት ለማሰራጨት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተካሄደ ነው። ከአቅርቦት አንጻር የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል። "ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር በርካታ ችግሮች እንዳሉ በዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ናቸው። ጥናቱን መሰረት በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል ። እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ከማድረግ አንጻርም ትኩረት ተሰጥቷል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም