በጅማ የነባሩ መናኽርያ አገልግሎት በጊዜያዊነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛወረ

78
ኢዜአ /ጥቅምት 29 / 2012  በጅማ ከተማ በነባሩ መናኽሪያ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት በጊዜያዊነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች መዛወሩን የከተማው የትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የባለስልጠኑ ኃላፊ አቶ ረሻድ አባሚልኪ ለኢዜአ እንደገለጹት በመናኽርያው ይሰጥ የነበረው አገልገሎት ከትላንት ጀምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲዛወር ተደርጓል። "የነባሩ መናኽሪያ በማስፋፊያ ግንባታ ላይ በመሆኑና በተለዋጭነት በመሰራት ላይ የሚገኘው የቴክኒክ ሜዳን ባለው ዝናባማ የአየር ጸባይ ወደ ስራ ማስገባት ባለመቻሉ አገልግሎቱ ወደሌሎች አካባቢዎች እንዲዛወር ተደርጓል " ብለዋል ። በነባሩ መናኽሪያ ይሰጡ የነበሩ አገልገሎቶች መካከል የሀገር አቋራጭ አውቶቢሶች መሳፊሪያ ወደ ከተማው የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራ፣ የአጋሮ መስመር ጉዞ ስታዲዬም አጠገብ፣ የሰቃ መስመር ጉዞ ረሃ ሆቴል አጠገብ መዛወራቸውን አስታውቀዋል። የሰርቦ መስመር ጉዞ አበጋዝ ሁቴል አጠገብ፣ የወልቂጤ መስመር ጉዞ በሬለምኔ ምግብ ቤት አጠገብ፣ የዴዶና ጭዳ መስመር ጉዞ ሳዳት ዳቦ ቤት አጠገብ ተደርጓል። የከተማው ስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ መናኽሪያ ሆነ በሚል በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለ መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ህብረተሰቡ በመገንዘብ  አገለግሎቱ ወደ ነባሩ መናኽርያ እስኪመለስ በጊዜያዊነት በተዘጋጁ ስፍራዎች በትዕግስት እንዲጠቀም መልዕክት አስተላልፈዋል ። የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ ህብረተሰቡ የነባሩ መናኽርያ ግንባታ እሰኪጠናቀቅ አገልገሎቱን በጊዜታዊ የስምሪት ስፍራዎች በመጠቀም ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም