ህዝበ ሙስሊሙ ሰላምን ከሚያደፈረስ አስተሳሰብ እራሱን እንዲያርቅ ተጠየቀ

64
ጅማ ኢዜአ ጥቅምት 29ቀን 2012፡- ህዝበ ሙስሊሙ ሰላምን ከሚያደፈርስ ከፋፋይ አስተሳሰብ እራሱን እንዲያርቅ ተጠየቀ 1ሺህ 494ኛው ነብዩ መሐመድ የልደት በዓል ዛሬ በጅማ ከተማ መድረሳ ጊቢ በድምቀት ተከብሯል። በክብረ በዓሉ ወቅት የትልቁ ሙኒር መስጂድ ኢማም ሺህ መሐመድ አባዲጋ እንደገለጹት የመውሊድ በዓል ማክበር ነብዩ መሐመድን ከጥልቅ መውደድ የሚመነጭ ምልክት ነው። “ነብዩን የምንወድ ከሆነ የእስልምና እምነት ባህሪ ካልሆነው ሰላም ከሚያደፈርሱ ከፋፋይ አስተሳሰብ ህዝበ ሙስሊሙ እንዲርቅ እጠይቃለው “ ብለዋል። ዑስታዝ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው በዘንድሮ መውሊድ በዓል የተደከመውን በሰላም አብሮ የሚኖር ባህላቸውን እንዲያንሰራራ የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል። “ይህም ለህዝባችን ሰላምና አንድነት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው “ ብለዋል። ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣት ዘሪቱ ሙህድን በሰጠችው አስተያየት በጅማ ከተማ እየተከበረ ያለው የመውሊድ በዓል ተራርቀው የነበሩ ሰዎችን አንድ ላይ ያገናኘ ጭምር በመሆኑ እንዳስደሰታት ተናግራለች ከዚህ በፊት የመውሊድ ባህልን የሚከፋፍል አስተሳሰብ የማራመድ ሁኔታ እንደነበር አስታውሳ በአሁኑ ወቅት ግን ህዝበ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር አብሮ ማክበር መጀመሩ የተሻለ መሆኑን ገልጻለች። የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መክዩ መሐመድ ህዝበ ሙስሊሙ ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላትን ለይቶ በማውጣት ከስህተታቸው እንዲማሩ በመስራት የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች በእኩልነት ፣በአንድነትና በሰላም እንድኖሩ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም