የሠላም እጦት ባለሃብቶች ስራቸውን እንዳያስፋፉ እንቅፋት ሆኗል

121
ጥቅምት 29 ቀን 2012  በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች የሚታየው የሠላም እጦት በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሃብቶች ስራቸውን እንዳያስፋፉ እንቅፋት መፍጠሩን ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ባለሃብቶች እንደሚሉት በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት እየተቀሰቀሱ ባሉ ግጭቶች ሳቢያ የንግድ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን አለማቻላቸውና ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን ይናገራሉ። በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ እንዳሉት ዘርፉ ከሌሎች ስራዎች ሰላም ፈላጊና ያለ ሰላም ምንም ዓይነት ተግባርን ማከናወን የማይቻልበት ነው። በቅርቡ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ለጉብኝት ወደተለያዩ ከልሎች የሄዱ ቱሪስቶች ያለ ፕሮግራማቸው ከሶስት እስከ አራት ቀን አንድ ቦታ እንዲቆዩም ከመሆኑ በተጨማሪ የበረራ ጊዜያቸው እንዲስተጓጎል ሆኗል። ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላም ጎብኚዎችን ወደ አገር ውስጥ ለመሳብ የሚደረገው ስራ ከፍተኛ ሃብት፣ ጉልበትና ጊዜ የሚጠይቅ ነው። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ እየተከሰተ ባለው የሰላም እጦት ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ ለመግባት ስጋት ስላላቸው የንግድ ስራቸው በሚፈለገው ደረጃ እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ወደ አገር ውስጥ የሚመጡት ቱሪስቶች የግጭት ስጋት አለባቸው ተብለው ወደሚጠቀሱ አገራት ሲንቀሳቀሱ ለህይወት መድህን የሚገቡት የኢንሹራንስ ዋጋ ስለሚጨምርባቸው አገሪቱን ለመጎብኘት ተቀዳሚ ምርጫቸው አያደርጉም። የሚመለከተው አካልም የግጭቱን መንስኤና በታዋቂ የመረጃ ምንጮች፣ በኤምባሲዎችና በሌሎች የመረጃ ዘዴዎች በፍጥነት ስለማያደርስ ጎብኚዎች የራሳቸውን መረጃ አጥርተው እስኪመጡ ቱሪዝሙ ይጎዳዋል ነው ያሉት። ‘’ተቃውሞ በራሱ ችግር ላይሆን ይችላል የተቃውሞ አገላለጻችን ከፍተኛ ችግር ያለውና አገርንም ይሁን ግለሰብን በጽኑ የሚጎዳ ነው ‘’ያሉን የሆቴልና መሰል አገልግሎት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት ናቸው። በተለይ መንገድ በመዝጋትና መሰረተ ልማቶችን በማቃጠል የሚደረግ ተቃውሞ በተዘዋዋሪ ጥቃት አድራሾች የራሳቸውን አገርና ቤተሰብ እየጎዱ መሆኑን መዘጋንት የለባቸውም ይላሉ። ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከጫማ መጥረግ እስከ ሆቴል ባለቤት ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማስታወስ። የማህበራዊ ሚዲያ፣ የብሮድካስትና የህትመት ሚዲያዎች ለጊዚያዊ ጥቅም የአገሪቱን መልካም ገጽታ የሚጎዱ መልዕክቶች ከማስተላለፍም መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል ነው የሚሉት። በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ወደ ጠረጴዛ አመጥቶ የመነጋጋር ልምዱ መዳበር አለበት ብለዋል። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የእርካብ አስመጪና ላኪ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ እመቤት ታፈሰ አሁን ካላቸው ስራ በተጨማሪ በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው አገራቸውን ለመጥቀም ዕቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ከክልል ወደ ክልል በነጻነት ተንቀሳቅሶ ለመስራት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው አገሬንና ራሴን ለመጥቀም ያለኝ ውጥን ላይ ስጋት አሳድሮብኛል ብለዋል። የሰላም እጦቱ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተዳምሮ ስራቸው ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል። የሰላሙ ባለቤትና በሰላም ማጣቱም ተጎጂው ራሱ ሕዝቡ በመሆኑ ለሰላሙ በጋራ ዘብ መቆም አለበት ሲሉም አሳስበዋል። መንግስትም ህግ የማስከበር ተግባሩን በአግባቡ መወጣት አለበት ነው ያሉት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም