አሜሪካ ወደ አፍሪካ የንግድ ልዑክ ልትልክ ነው

69
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 አሜሪካ በአፍሪካ የምታካሂደውን የቢዝነስ ሥራ ለመገምገም የሚያስችል የእውነት አፈላላጊ ቡድን ወደ አፍሪካ ልትልክ ነው። አሜሪካ በአፍሪካ ያላትን የቢዝነስ ተሳትፎ በተመለከተ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለማማከር ከተቋቋመው ምክር ቤት የተውጣጣው ቡድን አገሪቱ በኢትዮጵያ፣ በጋና፣ በኮትዲቯርና በኬንያ ያላትን የቢዝነስ ተሳትፎ በዝርዝር ይመለከታል ተብሏል። የቡድኑ መሪ የአሜሪካ የንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዊልቡር ሮስ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ከቀናት በኋላ ለማድረግ ወደ ጋና ያቀናሉ ነው የተባለው። ሌላኛው ቡድን ደግሞ የምክር ቤቱ ባልደረባ በሆኑት ጊልበርት ካፕላን አማካኝነት በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በኮትዲቯር ተመሳሳይ የአሜሪካ የቢዝነስ ሥራዎችን ይመለከታል። ጉብኝቱ ቡድኑ በአፍሪካ ያሉ የአሜሪካ ኢንቨስትመንትና የቢዝነስ ሥራዎች ያሏቸውን አማራጮችና የሚገጥማቸውን ችግር ለመለየት ይጠቅማል ተብሏል። የሚገኘውን መረጃም ለፕሬዝዳንት ትራምፕ በማቅረብ አሜሪካ ከአገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚረዳ ነው የተገለጸው። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን የንግድና የቢዝነስ ግንኙነት ለማጠናከር የወጠኑትን ዕቅድ እውን ለማድረግ እንደሚያግዝም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ የላከው መረጃ ያሳያል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም