ባህልንና እሴትን መሰረት ያደረገ ሳይንሳዊ ጥናት ላይ ማተኮር ለአገራዊ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ያግዛል - ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

70

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 28/2012 ልማትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ይቻል ዘንድ በአገሪቱ ባህልና እሴቶች ላይ የተመሰረቱ ሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ አትኩሮ መሥራት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

አገር አቀፍ የሳይንስ ሳምንት ''ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና" በሚል መሪ ሐሳብ  እየተከበረ ይገኛል።

ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በተሰናዳው መርሃ ግብር ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች  አመራር አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንደተናገሩት በአገሪቱ የሚካሄዱ ጥናቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በህዝቦች ባህልና እሴቶች ላይ የተመሰረቱ ሊሆኑ ይገባል።

ሳይንሳዊ ጥናቶች አገራዊ ባህልንና እሴትን ማእከል ያደረጉ ከሆነ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት የሚያስችል አቅም ይኖራቸዋል፤ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት ለማሳደግና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥም ያግዛሉ ባይ ናቸው ፕሬዚዳንቷ።

ጥናቶቹ ይህንን መሰረት የሚያደርጉ ካልሆኑ ግን ጥናቶቹ ችግር ከመፍታት ይልቅ ለችግር መርስኤ እየሆኑ እንደሚመጡ ነው ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ  ያሳሰቡት።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም በበኩላቸው ለችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ሳይንሳዊ የሆነ አስተሳሰብና አሰራርን ባህል ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሳይንስን ባህል ለማድረግ  ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች በዜጎች የእለት ተእልት እንቅስቃሴ  ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት ለችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ መሆን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ ህጻናት ተማሪዎች ሳይንስንና ምርምርን በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ እየጎለበተ ምርምርን ባህል አድርግረው ያድጉ ዘንድ ደረጃቸውን የሚመጥን የፈጠራ ስራ እንዲሞክሩ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠርከሚመለከታቸው አካላት ጋር  እየተሰራ እንደሆነም ፕሮፌሰር ሂሩት አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊና  መልካም የመማር ማስተማር ድባብ እንዲፈጠር፣  ምክንያታዊ፣ ተመራማሪና አርቆ አሳቢ ዜጋ ለማፍራት የሚኒስቴሩ የበኩሉን ድረሻ እየተወጣ እንደሆነም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንሰ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማሪያም በበኩላቸው የኢትዮጵያን ምጣኔ ኃብት ለማሳደግ አገሪቱ ያላትን ውስን ሃብት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አስደግፎ ማጥናት ይገባል ብለዋል።

ይህንን ለማድረግ በአገር ውስጥ ያሉ ሃብቶችን መለየት፣ የህብረተሰቡን ባህልና እሴት መርምሮ ማወቅ፣ ከዚህ በፊት የተሰሩ አገር በቀል ስራዎችን እንደመነሻ ለመጠቀም የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በዚሁ ዝግጅት ተማሪዎች የፈጠራ ስራዎቻቸውን፤ ተመራማሪዎች ደግሞ የምርምር ውጤቶቻቸውን  አቅርበዋል።

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ተማሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የፈጠራ ስራዎቻቸውን ሌሎች እንዲያዩላቸው መደረጉና ለወደፊት ከዚህ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ እንዳበረታታቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም