በርካታ መስሪያ ቤቶች ለሳይበር ደህንነት የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆኑ ተገለጸ

68
ጥቅምት 28/2012 በርካታ የፌዴራልና ክልል መስሪያ ቤቶች ለሳይበር ደህንነት የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ። ሳይበር የሰው ልጅ የእርስ በእርስ ግንኙነት ማደግ የወለደው የቴክኖሎጂ ውጤት ሲሆን በመሰረተ ልማት፣ በመረጃ፣ በግለሰቦችና በማህበረሰብ መስተጋብር እውን እየሆነ ነው። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ብሄራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንትን አስመልክቶ ዛሬ ለሁሉም ሚኒስቴሮች የግንዛቤ መድረክ አዘጋጅቷል። በኤጀንሲው የኢንፎርሜሽን ደህንነት ባለሙያ አቶ ናምሩድ ከሰተ ብርሃን በመድረኩ ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍ አብዛኛውቹ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ለሳይበር ደህንነት የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ነው። በ2011ዓ.ም በተደረገ የዳሰሳ ጥናትም 43 የፌዴራልና የክልል ተቋማትን ያሳተፈ አገር አቀፍ የቁልፍ ተቋማት የሳይበር ደህንነት  ክፍተቶች የሚስተዋሉባቸው እንደሆነ ተገልጿል። በተቋማቱ፣ ዝቅተኛ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊናና ትኩረት፣ የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎች አለመኖር፣ የሳይበር ደህንነት አመራርና አስተዳደር ስርዓት አለመኖርና የሳይበር ደህንነት ማዕቀፍ አለመኖር ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንዲሆን ማድረጉን ተነስቷል። በመሆኑም፣ ተቋማትን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሳይበር ደህንነት እንደ አገር ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና በተቋማቱ የሳይበር ደህንነት አመራርና አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ነው አቶ ናምሩድ ያነሱት። በየደረጃው ጠንካራና ተከታታይ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ስርዓትን መዘርጋት፣ በዘርፉ የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትና የዘመነ የሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ መዘርጋት የተቋማቱ የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባም ተጠቁሟል። ከተለያዩ ሚኒስቴሮች የተገኙት ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ለሳይበር ደህንነት ትኩረት እንዲሰጡ ያስገነዘባቸው እንደሆነ ገለጸዋል። በቀጣይም ተቋማቱ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህነነት ኤጀንሲ ጋር በሳይበር ደህንነት ዙሪያ በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውና በኤጀንሲው በኩል የግንዛቤ ስልጠናዎች እንዲሰጧቸው ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። የሳይበር ጥቃቶች የአገር ሉዓላዊነትን የሚጥስ፣ ማህበራዊ ቀውስና የፖለቲካ ቀውስ  የሚያስከትልና የአገርን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው። የሳይበር ጥቃት በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በተቋማትና በአገር ደረጃ የሚፈጸሙ ሲሆን የጥቃት ፈጻሚዎቹ ዋና ዋና አላማዎች ገንዘብ ማግኘት፣ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ መፍጠር፣ መረጃንና መሰረተ ልማቶችን ማውደም ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም