የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት በራስ የሚተማመኑ ሴቶችን ለመፍጠር እየተሰራ ነው - አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት በራስ የሚተማመኑ ሴቶችን ለመፍጠር እየተሰራ ነው - አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
109
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2012 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሴት ተማሪዎች የሚያደርገውን የቁሳቁስ ድጋፍ ለማሟላት የፋይናንስ እጥረት እንደገጠመው ተገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ 'ሴቶች ለሁለንተናዊ እድገት መሰረቶች ናቸው' በሚል መሪ ሐሳብ ከሴት ተማሪዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መክርዋል።
በውይይቱም ተቋሙ ሴት ተማሪዎች በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ወዳልተፈለገ ህይወት እንዳይገቡ ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በርካታ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ በዩኒቨርሲቲው የሴቶች፤ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ማተቤ ታረቀኝ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድጋፍ የሚፈልጉ ተማሪዎች ቁጥር በመበርከቱ ተቋሙ የሚያደርገውን ድጋፍ ማድረግ እንዳይችል ተግዳሮት እንደሆነበት ተናግረዋል።
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት በራስ የሚተማመኑ ሴቶችን ለመፍጠር የፋይናንስ ችግር ትልቅ ተግዳሮት በመሆኑ በዚህ ዙሪያ መስራት ለሚፈልጉ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በራችን ክፍት ነው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል ።
ሴቶች በማህበራዊው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ሴቶችም ኢትዮጵያ በጀመረችው የእድገት ጉዞ መሪ ተዋናይ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።