የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የሚያደርገውን የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ትብብር ያጠናክራል

66
ጥቅምት 27/2012 የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በቴክኖሎጂና በፈጠራ ሥራ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኅብረቱ ልዑክ ቡድን መሪ ራኔሪ ሳባቱቺ ገለጹ። የአፍሪካ ኅብረት ከአውሮጳ ኅብረት ጋር በመሆን 'በአፍሪካ ፈጠራና ቴክኖሎጂ' ላይ በአዲስ አበባ መክሯል። ተቋማቱ ባለፈው መስከረም በፈጠራ ሥራና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ደርሰዋል። አጋርነቱ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ማዕከላትን እርስ በእርስ ለማስተሳሰርና አዲስ የገበያ ዕድል ማፈላለግ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ተብሏል። ጎን ለጎንም በዘርፉ ከሚሰሩ አካላት ጋር አጋርነትና ትስስር መፍጠር እንዲሁም ዕውቀትና ልምድ መለዋወጥ ላይ ያተኩራል። በተለይም በጥቃቅንና አነስተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ የሚሰሩ የዘርፉ አንቀሳቃሾችን አቅም ለማሳደግ ነው የታሰበው። ይህን ተከትሎ በአፍሪካ ኅብረት የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሙቸንጋም 'አጋርነቱ የሁለቱን ተቋማት ትብብር እያጠናከረው ነው' ብለዋል። በተለይም ቴክኖሎጂን ማስፋፋት የሚያስችሉ በአውሮጳና በአፍሪካ የጋራ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ማዕቀፍ ለመመሥረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተመሳሳይ በዘርፉ የሚሰሩ አፍሪካዊያን የአቅም ግንባታ እንዲደረግላቸውና በአገራቸውም የገበያ ዕድል እንዲፈጠርላቸው እየያገዘ መሆኑን ጠቁመዋል። በዘርፉ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግና የፖሊሲ አውጪዎች ውሳኔዎች ላይ አዎንታዊ ጫና ለማሳደር የሚያስችል ውይይት ማስፋፋቱን ተናግረዋል። ያም ብቻ ሳይሆን የዘርፉን ችግሮች ነቅሶ ለማወጣትና የፈጠራ ሥራን ሊያሳልጥ የሚችል ሥርዓት ለመዘርጋት በጋራ እየተሰራ እንደሆነ ነው የጠቆሙት። ለአፍሪካ ኅብረት የአውሮጳ ኅብረት ልዑክ ቡድን መሪ ራኔሪ ሳባቱቺ እንደተናገሩትም የአውሮጳ ኅብረት ከአፍሪካ ጋር ያለውን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ትብብር ማጠናከር ይሻል። የአውሮጳ ኅብረት አባል አገራት የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል መሆናቸውን ጠቁመው 'የዘርፉን ባለሙያዎቸ ወደ አውሮጳም ጭምር በመውሰድ ለማብቃት እንሰራለን' ብለዋል። የአውሮጳ ኅብረት ለአፍሪካ አገራት ባዘጋጀው የጥናትና ምርምር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግም ጭምር የዘርፉን ምርምሮች ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይም ይህን አይነቱን አጋርነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የአውሮጳ ኅብረት በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያረገገጡት። በመስከረም 2012 ዓ.ም የተፈረመው የትብብር ማዕቀፉ በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ2013 ዓ.ም ግንቦት ላይ ይጠናቀቃል። ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የሚለቀቀው የመርኃ ግብሩ የገንዘብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ይሸፍነዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም