የአብሮነት የንቃት መንገድ፡- መደመር

2040
                      በፍጹም እሸት  ሽመልስ             ይህ መጠነኛ የመጽሀፍ ዳሰሳ አጠር ያለ ጥቅል ምልከታ እንጂ በዋቢ ተደግፎ የመደመርን ዕሳቤ ከሌሎች ደጋፊና ተጻራሪ ፍልስፍናዎችና ሀሳቦች ጋር በማወዳደርና በማነጻጸር የቀረበ ጥልቅና ሰፊ ዳሰሳ አለመሆኑ ልብ ይባል፡፡ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገውም "መጽሀፉ ምን ይዞልን መጣ?" በሚል መነሻ "መደመር" እንደ መጽሃፍ ከቅርጽ፣ ከአቀራረብና ከይዘት አኳያ ምን እንደሚመስል በአውዳዊ ትንታኔ አስደግፎ ማሳየት ነው፡፡                  ለመንደርደር የመፅሐፉ ደራሲ "የመደመር መምህሬ ተፈጥሮ ናት፤ ጠመኔዋ የልጅነት መንደሬ በሻሻ፤ ሰሌዳዋ ደግሞ የልጅነት አእምሮዬ ነው" በማለት የመደመር ዕሳቤ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ በተፈጥሮ አማካይነት ወረቱን አዕምሯቸው ውስጥ ያከማች እንደነበር ይነግሩናል፡፡ ከተል አድርገውም የመደመር ዕሳቤ ደራሲው ልጅ ሳሉ ልጅ የነበረ፣ ወጣት ሲሆኑ አብሮአቸው የፈረጠመ፣ ሲጎለምሱና አዋቂ ሆነው አገራዊ ኃላፊነትን በተለያየ ደረጃ ሲቀበሉ ደግሞ አብሮአቸው እየበሰለ መጥቶ ለሚወዷት አገራቸው የሚመርጡት አስተሳሰብ ለመሆን መብቃቱን ከትበውልናል፡፡ ደራሲው "ለምወዳት አገሬ የምመርጠው ዕሳቤ ነው" የሚሉትን "መደመር" መጽሀፍ በ300 ብር ገዝቶ ማንበብ ምን የሚያስገኘው ትሩፋት አለ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ "ከመንደር እስከ ዓለም አቀፍ ያለ ምልከታዬ ላይ አንዳች ነገር ለመጨመር" የሚል መልስ መከተሉ እሙን ነው፡፡ መጨመር ደግሞ መደመር የተገነባበት አንዱ ጡብ ነው፡፡ በአመክንዮ እና በእውነት ላይ ተመስርቼ ልሟገት የሚል መልስ ቢሰነዘርም ይህም በራሱ የመደመር እሳቤ አካል ነው፡፡ መጽሀፉን ገዝቶ ማንበብ ባለ እውቀት ላይ አንዳች ነገር ለመጨመር ከማገዝ ባሻገር ነገን "የተማረ የሰው ኃይል ለማየት ያስችላል" የሚል መልስም ትክክለኛ ነው፡፡ ምክንያቱም የመጽሐፉ ገቢ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ትምህርትን ለማስፋፋት የሚውል መሆኑ ተመልክቷልና! ስለዚህ መደመር መጽሐፍ ሲነሳ በተደራሲያን አእምሮ ሊፈጠር የሚችለው "የአገሪቱን ትልቁን ስልጣን የተቆናጠጠ መሪ ምን አለ?" የሚለው ተገዳዳሪ ሀሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ መጽሐፉ አንዳች ነገር ለመደመር ታስቦ የተጻፈ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በእርግጥ መጽሐፉ አንዳች ነገር ከመደመር የራቀና የጠለቀ ምልከታ ያነገበ መሆኑ የማይታበል ነው፡፡ ምክንያቱም መደመር ከተፈጥሮ ህግና ኃይል እንዲሁም ከሰው ልጅ ተደማሪ ፍላጎትና አቅም ጋር ተሰናስሎ መዳረሻ ግቡን ብልጽግና ያደረገ ትልቅ ዕሳቤ ነው፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ "መደመር" መጽሀፍ በአራት አበይት ክፍሎች፣ በ16 ምዕራፎችና በ280 ገፆች (በሮማን ቁጥር የተቀመጡትን ከምስጋና እስከ መግቢያ ያሉ 8 ገጾች ሳይጨምር) ተቀንብቦ 300 ብር ዋጋ ተቆርጦለት ለንባብ የበቃ የፖለቲካ መጽሀፍ ነው፡፡ "መደመር" ለንባብ እስከበቃበት ደረጃ የደረሰውም "በመደመር አስተሳሰብና መንገድ" ነው ይሉናል ጸሀፊው፡፡                         መቃተት ለጸሐፊው መጽሀፍ የሚጽፍ ሰው ነፍሱ ስለ አንዳች ነገር መቃተቷ አይቀሬ ነው፡፡ ሀሳቡን በመጽሐፍ ያኖር ዘንድ ስለተነሳበት ጉዳይ ያወጣል፤ ያወርዳል፤ ያብሰለስላል፡፡ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ ፍለጋ ይባዝናል፡፡ ይከትበው ዘንድ የተነሳበትን ሀሳብ በተጨባጭ ዕውነታዎች ፈትሾ ለማህበረሰቡ አንዳች ነገር ለማበርከት ይቃትታል፡፡ የመደመር ጸሐፊም መጽሐፉን ለንባብ በበቃበት መንገድ ቀንብቦ በማቅረብ ሂደት ውስጥ በብዙ አገራዊ ጉዳዮች ሲቃትቱ እንደነበር መረዳት አያዳግትም፡፡ መቃተታቸውንም በመጽሐፉ ውስጥ ከሰፈሩ ሀሳቦች እየመዘዝን መመልከት እንችላለን፡፡ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ያስተውሉ የነበሩት የተፈጥሮ ኃይልና ሀብት ድምር ቀለማት ተራ ግጥምጥሞሽ ሳይሆን ለአንዳች የጋራ ተልዕኮ የተደመረ  መሆኑን ያብሰለስሉ እንደነበር ሲነግሩን መቃተቱ ከልጅነታቸው እንደጀመረ እንረዳለን፡፡ የመደመር ማበልፀጊያዎች ፀሐፊው በተለያዩ ጊዜያት ያዘጋጃቸው የሰልጠና ሰነዶች፣ ለድርጅት አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት ያቀረቧቸው የመወያያ ጽሁፎች፣ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወዘተ መሆናቸውን ከመጽሀፉ መቅድም ስናነብ ደግሞ መቃተቱ አብሯቸው ስለማደጉ እንገነዘባለን፡፡ የመቃተት ደረጃውን ከፍ አድርገን ማየት ካለብን ደግሞ ስለምን ኋላ ቀር ስርአት በለያችን ላይ ተጫነ? ፤ ያሉን መልካም ወረቶች ላይ እየደመርን መሻገር ሰለምን ተሳነን? ፤ ፍላጎቶቻችንን ከአቅማችን ጋር አጣጥመን መጓዝ ለምን አልቻልንም? ፤ ግራ በገባው ፖለቲካ ወዲያ ወዲህ መላጋታችንን ለምን ማቆም አቃተን? ፤ የኢኮኖሚ ስብራታችን ስለምን ወጌሻ አጣ? ፤ የውጪ ግንኙነታችንስ እንዴት ነው የበለጠ መላቅ የሚችለው?  ወዘተ በሚሉ በእውቀት ላይ በተመሰረቱ ጉዳዮች ሲቃትቱ መቆየታቸውን ከመጽሐፉ መረዳት እንችላለን፡፡                           ቅንብረ ውበትና አቀራረብ መጽሀፉ ከፊት ለፊት እስከ ጀርባ ሽፋኑ፣ ከመግቢያ እስከ መውጫው ባልተወሳሰበ ቅንብር የቀረበ ነው፤ የሚረብሽ ነገር የለውም፡፡ የፊት ሽፋኑ ላይ አንዳች ፈገግታውን ሊያጋባብን የፈለገ የሚመስል ሰው (የመጽሀፉ ጸሀፊ) ገጽታ ይታያል፡፡ ይህም ደራሲው በመጽሃፉ የፊት ሽፋን ላይ ስለምን መልክአ ምድር፣ ሰንደቅ-ዐላማ፣ የመደመር ምልክት ወይም ሌላ የሽፋን ምስል አላኖሩም የሚል ጥያቄ እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ጥያቄአችን በዚህ የሚያበቃም ላይሆን ይችላል፡፡ "ይህ ሰው ማን ነው?" የሚል የሰውዬውን የኋላ ማንነት ለማወቅ የሚያነሳሳ ጥያቄም ይፈጠራል፡፡ ይህም መለስ ብለን የደራሲውን የቀደሙ ስራዎች ለመጎብኘትና ለመፈተሽ ብርታት የመፍጠር አቅም አለው፡፡ የውስጥ ገጽ ቅንብሩም ዕይታን በሚስብና ለንባብ በሚጋብዝ መልኩ የተሰናዳ ነው፤ አልታጨቀም፡፡ “መደመር” ለመጽሀፉ ርዕስ ተደርጎ የተሰጠ ነው። ይህን የመጽሀፍ ርእስ ጸሀፊው በተደጋጋሚ በሚያነሷቸው ሀሳብ ገዥነት ባናውቀው ኖሮ “ለንባብ የሚጋብዝ ርእስ ነው ወይ?“ ብለን ብንጠይቅ መልሱ “በጭራሽ“ የሚል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መደመር የሚለውን ቃል የምናውቀው ከሂሳብ ስሌት ጋር ከተዋወቅንበት ጊዜ አንስቶ ነው። አቅልለን እናየዋለን፤ ቀሎ ስለመጣ። በአቀራረብ ረገድም "መጽሀፉ ከአካዳሚያዊ ዓላማ ይልቅ ለፖለቲካ ዓላማ የተጻፈ በመሆኑ አካዳሚያዊ አቀራረብን ስራዬ ብሎ የተከተለ አይደለም" እንዲል መደመር፤ መጽሀፉ ኢመደበኛ አጻጻፍን ተከትሎ የቀረበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ደራሲው በዋና ዋና ግብአትነት የተጠቀሟቸውን አስረጅ ሀሳቦች በዋቤ መጻህፍት ስር ብቻ እንዲጠቀሱ መደረጋቸው የአጻጻፍ ስልቱ ኢመደበኛ ለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ መጽሀፉ በቀጥታ "መደመር" እንዲህ ነው እንዲያ ነው ወደሚል ብያኔያዊ ምልከታና ትንታኔ ከመግባቱ በፊት የዕሳቤው መነሻ ስለሆኑት የሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ የሰው ልጅ ተደማሪ ፍላጎቶችና ስለሰው ዐቅም መዳሰሱ የአቀራረብ ስልቱን አንድ እርምጃ ከፍ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡ ከአቀራረብ ጋር አያይዞ ማንሳት የሚቻለው ሌላው ጉዳይ የቋንቋ አጠቃቀም ነው፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሙ ጉራማይሌ አለመሆኑና ወጥነት የተስተዋለበት መሆኑ ደራሲው ለቋንቋ አጠቃቀም የሰጡትን ትኩረት ያመላክታል፡፡ በመጽሀፉ የመግቢያ መቋጫ ላይ እንደተመለከተውም "በመጽሀፉ ውስጥ በተቻለ ዐቅም ቃላትን አገራዊ ፍች ሰጥቶ ለመጠቀም ተሞክሯል፡፡" ይሉናል፡፡ በተጨማሪም  ደራሲው ለተጠቀሟቸው ቃላት አገራዊ ፍች ለመስጠት በሚያደርጉት ሂደት ውስጥ የቃላቱ ትርጉም በተሳሳተ መንገድ እንዳይወሰድ ጥንቃቄ ለማድረግ ሲባልም ቃላቱን በየተጠቀሱበት ቦታ ብያኔ ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡ አንድ ማሳያ መጥቀስ ቢያስፈልግ በገጽ 41 ስለወረት የተሰጠውን ሁለንተናዊ መነሻ አቅም የሚል ብያኔ ማንሳት ይቻላል፡፡ በጽሁፉ ውስጥ ብያኔ ያልተሰጣቸው ወይም በደምሳሳው የተጠቀሱ ቃላት ደግሞ በሙዳየ ቃላት የፍች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡                                አዲስ መነጽር መጽሐፉ ቀደም ሲል ነገሮችን የምንመለከትበትን መነጽር መጀመሪያ ማውለቅ እንዳለብን ይነግረናል፡፡ "ዓለምን በርዕዮተ ዓለማዊ የብያኔ መነጽር ከማየት የሚቀድም ነገር አለ" የሚለን መደመር መጀመሪያ "የሰው ልጅ ተፈጥሮ" ላይ ማተኮር እንደሚገባ ያስረዳል፡፡ የሰው ልጆችን ስለሚጠቅም ማንኛውም ሀሳብ ከማውጠንጠን በፊት ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ ማሰብ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁመናል፡፡ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ማወቅ ደግሞ "በአንድ በኩል ፍላጎቱንና ምኞቱን ተረድቶ ይህንኑ ለማሳካት፣ በበሌላ በኩል አቅሙን ለመረዳትና አሟጦ ሊጠቀምበት የሚያስችለውን አግባብ ለመተለም ያስችላል፡፡" ባይ ነው፡፡ የመደመር መነጽር የሰውን ልጅ መሰረታዊ ፍላጎትና አቅም በመዳሰስና በመመርመር ይጀምራል፡፡ ውስጣዊ የመጉደል ስሜቶች የሚፈጥሯቸው ህልውናን የማረጋገጥ ፍላጎቶችን "ቀጥተኛ ፍላጎት" እና "ተዘዋዋሪ ፍላጎት" በሚሉ ሁለት መሰረታዊ ክፍሎች ከፍሎ ይመለከታቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ራስን ከጥቃት ከመከላከል ጋር የሚታይ ሲሆን ሁለተኛው የፍላጎት አይነት ደግሞ በውስጡ የስጋ፣ የስም ወይም የክብር እና የነፃነትን ፍላጎቶችን ያቀፈ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መደመር "ከቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ፍላጎት ቀድሞ መሟላት ያለበት የትኛው ነው" የሚል ዕይታን ወደጎን ትተን ወይም ያንን መነጽር አውልቀን "ሁሉም አይነት ፍላጎቶች ተደማሪ ባህርይ አላቸው" በሚል የዕይታ መነጽር መመልከት እንደሚገባ ያሳያል፡፡ የሰው ተፈጥሮ ተደማሪ በሆኑ ፍላጎቶቹ አንፃር መታየት አለበት የሚል ሀሳብ የሚሰነዝረው መፅሀፉ "ሰው በማህበራዊና ፖለቲካዊ ማንነት የሚገለጥ እንሰሳ ነው" የሚለውን የፖለቲካ ምሁራን ትንታኔ በሌላ መልኩ መመልከት እንደሚገባም አሳይቷል፡፡ በሌላ መልኩ "ለአገር ውስጥ ችግሮቻችን አገር በቀል መፍትሄዎችን ከመፈለግ ይልቅ ወደ ውጭ ማማተራችን ችግሮቻችን መልካቸውን እንዲቀይሩ እንጂ እንዲወገዱ አላደረገም" የሚል ሀሳብ ከመጽሀፉ ገጾች ስናነብ ወደ “ውስጥ መመልከት እንዴት ነው? አገር በቀል መፍትሄስ ከወዴት ነው?" ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፤ የቀድሞ መነጽራችንን እንድናወልቅ ይገፋፋናል፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎቻችን መልስ ለማግኘት ግን መፅሀፉን ማንበብ የግድ ይላል፡፡                            ጥቂት ስለ ዕሳቤው ጸሀፊው "ኢትዮጵያዊ ዕሳቤ" እንደሆነ የሚገልጹልንን መደመር ያመነጩ ሁለት ገባሮች መኖራቸውን ይነግሩናል፡፡ እነዚህም የህብረተሰባችን የልብ ትርታ የተቃኘባቸው እሴቶቻችንና የተፈጥሮ ህግጋት መሆናቸውን ያስረዱናል፡፡ ይህም "መደመር" አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ከሚል ቀላል ሂሳባዊ ስሌት የላቀና የራቀ መሆኑንና በተፈጥሮና በሰው ልጅ መካከል በሚፈጠር መስተጋብር ውስጥ ራሱን የሚያይ መሆኑን እንረዳለን፡፡ "መደመር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎችን ጨምሮ ሁሉንም ግላዊ እና ማህበረሰባዊ የሂወት ዘይቤን የሚነካ ዕሳቤ ነው፡፡" በማለት የመጽሐፉ ጸሐፊ የመደመር የብያኔ ወሰን ምን ያህል ሰፊና ጥልቅ እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ ቀጠል አድርገውም "መደመር አገራዊ አውድን መሰረት አድርገን ችግሮቻችንን እንዴት ልንፈታ እንችላለን ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ዕሳቤ ነው፡፡" ሲሉን የመደመር ብያኔ ከአገራዊ ነባራዊ ሁኔታ የሚመነጭ መሆኑን እየጠቆሙን እንደሆነ ልብ እንላለን፡፡ "የቤቱን ቁልፍ ጨለማ ውስጥ ጥሎ ብርሃን ያለበት ቦታ ላይ ለመፈለግ እንደሚጣጣር ሰካራም" ያለ አካሄዳችን ዋጋ እንዳስከፈለን ያብራራል፡- መደመር፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 7 እና 8 አስርታት የተከተለችው አገራዊ አቋም በምዕራባዊያንና ምስራቃውያን አስተሳሰብ የተቃኘ ሆኖ መቆየቱ እና ወደ ውጭ ያማተርንበትን ያህል ወደ ውስጣችን መመልከት አለመቻላችን ለአገራችን ችግሮች አገር በቀል መፍትሔዎችን እንዳናማትር እንዳደረገንም ይጠቅሳል፡፡ ይህንን አይነቱን አካሄድ በመግታት ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ መሰረታችንን ሳንለቅ ሀገራዊ አውድን መሰረት በማድረግ ችግሮቻችንን እንዴት መሻገር እንደምንችል የሚያመላክት ዕሳቤ መሆኑም ተብራርቷል፡፡ መደመር ከችግር ትንተና አኳያ አገር በቀል ቢሆንም ከመፍትሔ አኳያ ከአገር ውስጥም ከውጪም ትምህርት በመውሰድ የተቀመረ መሆኑን ፀሐፊው ይጠቅሳሉ፡፡ ዋነኛ ዓላማውም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበቻቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎች ጠብቆ በማስፋት፣ የተሰሩ ስህተቶችን ማረምና የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህ የሚነግረን አንድ እውነታ መደመር ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን አሰናስሎ የሚመለከት መሆኑን ነው፡፡ ይህ ትላንትን ዛሬንና ነገን ያሰናሰለ ዕሳቤ ግቡን ሊመታ የሚችለው በሰዎች የተነሳሽነት መጠን መሆኑን የሚያጠይቀው መጽሀፉ የተነሳሽነት መጠኑንም በሶስት ደረጃዎች ከፍሎ ይመለከታል፡፡ እነዚህም አልፎ ሂያጅነት (መደመርን በሩቅ አይቶ ማለፍ) ፣ እንግድነት (ከአልፎ ሂያጅነት ተላቆ ወደ ቤት መግባት) እና ቤተኛነት (መደመርን የራስ ዕሳቤ ማድረግ) ናቸው፡፡ ሶስተኛው የተነሳሽነት ደረጃ የዕሳቤው ግብ መምቻ ሁነኛ መንገድ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አገራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብር እና ብልጽግና ዋና ዋናዎቹ የዕሳቤው እሴቶች ሲሆኑ ዋልታ ረገጥነት፣ ጊዜ ታካኪነት፣ አቅላይነት፣ ሙያን መናቅ፣ ሞገደኝነት፣ አድር ባይነት፣ ህሊና ቢስነት እና ልግመኝነት የአስተሳሰብና የግብር ሳንካዎችና ቀይ መስመሮች መሆናቸውም በመጽሀፉ ተተንትኖ ቀርቧል፡፡                         ከብቸኝነት ጉድለት ወደ ክሱትነት ምንም ነገር በራሱ ምሉዕ አይደለም የሚለው መደመር ወደ ሙሉዕነት ለመምጣት ከአካባቢ ጋር መስተጋብዊ ግንኙነት መፍጠር የግድ እንደሚል ያስገነዘባል፡፡ ሰዎች ለምሉዕነት በሚደረግ ጉዞ ውስጥ አስፈላጊ የሆነውን አካባቢያዊ ግንኙነት ማድረግ ሲሳናቸው ወይም ሲቸገሩ "የብቸኝነት ጉድለት ይከሰታል" ይለናል፡፡ ይህ የብቸኝነት ጉድለት በሰው ልጆች ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳለው በመጠቆም፡፡ የብቸኝነት ጉድለትን የመሙላትና ወደ ምሉእነት የመምጣት የሰዎች ብርቱ ፍላጎትና ጥረት ጉድለታቸውን የሚሞሉበትን ነገር እንዲያማትሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ጥረታቸው ማህበራዊ አደረጃጀቶችን እንደፈጠረላቸውም መደመር ያምናል፡፡ ማህበራዊ ደረጃጀቱ አንዱ የብቸኝነት ጉድለትን የመሙያ ስልት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ ህልውናውን አስጠብቆ ለመቆየት ርዳታና ትብብርን የሚሻ ፍጡር መሆኑን የሚነግረን መደመር የብቸኝነት ጉድለትን ለመሙላት የሚደረግ ጥረት የሰው ልጆችን ሁለንተናዊ እድገት የማረጋገጥ አቅም አለው ብሎ ይሞግታል፡፡ "የሰው ልጅ ለብቻው ራሱን መመገብም ሆነ ራሱን ከአደጋ በዘላቂነት ጠብቆ በህይወት መቆየት አይችልም፡፡" የሚል ሃሳብ በመጽሀፉ ሶስተኛ ምእራፍ ውሰጥ ሰፍሮ ስናስተውል አንድም ሰው ማህበራዊ ፍጥረት መሆኑን ያስታውሰናል፤ ሁለትም ሰው በብዙ ነገር ብቻውን የሆን ዘንድ መልካም አለመሆኑን ያስረዳናል፡፡ የብቸኝነት ጉድለትን ለመሙላት ከአካባቢ ጋር ለሚደረግ መስተጋብር ፉክክርና ትብብር መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን መደመር ያሰምርበታል፡፡ ነገር ግን ፉክክርና ትብብር ሚዛን አጥተው አንዱ ሲያይል ሰዎች ከአካባቢያቸው ጋር የሚያደርጉት መስተጋብር ስለሚቋረጥ የብቸኝነት ጉድለት ይከሰታል ይለናል፡፡ ይህ የብቸኝነት ጉድለት የፉክክርና የትብብርን ሚዛን በመጠበቅ እንዲሁም የመደመር የትርጓሜ መሰረታውያን ለሆኑት መሰብሰብ፣ ማከማቸትና ማካበት ትልቅ ዋጋ በመስጠት ሊሞላ ይችላል፡፡ በጥቅሉ ከብቸኝነት ጉድለት ለመውጣት፣ ክሱትነትን ለማረጋገጥና ህልውናችንን ለማስቀጠል እንችል ዘንድ አቅም የምናገኝበት የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ወረት (ሁለንተናዊ መነሻ ዐቅም) ማፍሪያ መንገድ "መደመር" ነው ይሉናል፤ የመጽሀፉ ደራሲ፡፡ ከብቸኝነት ጉድለት ለመላቀቅ የጋራ ግብ ማስቀመጥና ለግቡ ስኬት በተነሳሽነት መስራት መሰረታዊ ነገሮች መሆናቸውን አጽንኦት ይሰጧቸዋል፡፡                                     ጭቆና ትልቁ የፖለቲካ ስብራት? በመደመር ዕሳቤ "ጭቆና" ትልቀቁ ስብራት መሆኑ ተመልቷል፡፡ ምን ማለት ነው? መልሱ በመፅኀፉ ተብራርቷል፡፡ ጭቆና የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት የሚውለውን ማንኛውንም ነገር እየነጠቀ ለሌሎች ሰዎች መሻት እንዲውል የሚያደርግ ጎታች ነገር መሆኑንም መጽሀፉ ያስቀምጣል፡፡ መደመር ጭቆናን "ሰው ወለድ ጭቆና" እና "መዋቅር ወለድ ጭቆና" በማለት በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ ሰው ወለድ ጭቆና ከሰዎች ክፉ ሀሳብና ህሊና የሚመነጭና በሰዎች ፍላጎትና እቅድ የሚተገበር ሲሆን የጭቆናው ማብቂያ ጨቋኞችን ታግሎ ድል በማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛውና ከመዋቅር ወይም ከስርዓት የሚመነጨውን የጭቆና አይነት ደግሞ "ሆን ተብሎ የማይከወን፤ ነገር ግን የተዘረጋው ተቋማዊ መዋቅር/ ስርዓት ሰዎችን መርጦ የሚያጠቃና ፍላጎታቸውን የሚያጓድል" ሲል ይገልጸዋል፡፡   ሁለቱንም የጭቆና አይነቶች ካሳለፍነው የፖለቲካ ታሪክ አኳያ የሚተነትነው መጽሀፉ በተለይ መዋቅር ወለድ ጭቆናን ለመመከት የቡድን ማንነትን ይዞ መታገል የቡድን አክራሪነትን በመፍጠር የአገርን ሰላም በማናጋት ዜጎች ተቻችለው እንዳይኖሩ ያደርጋል የሚል መከራከሪያ ያነሳል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለውን አፀፋዊ ጭቆና (የዐይን ለጠፋ ዐይን ማጥፋት) አይነት አካሄድም ከብርሃን ይልቅ ወደ ጨለማ የሚመልስ በመሆኑ "መሞከር የለበትም" ይላል፡፡ ይልቁንም የችግሮቹን/የጭቆናዎቹን ልክ በጥናት በመለየት በሲቪልም በፖለቲካም ድምር አቅም የሚተገበር መፍትሔ መስጠት የሚኖረውን አስፈላጊነት ያስረዳል፡፡   ጭቆናን በሁለንተናዊ መልኩ አስወግዶ ህዝብን የአገር ባለቤት ለማድረግ ከነ እንከኑ ከዲሞክራሲ የተሻለ አማራጭ ስርዓት እንደሌለም መደመር ያምናል፡፡ ምክንያቱም ዲሞክሲ የስልጣን ቅቡልነትን ከዘር ሀረግ፣ ከጉልበት ወይም ከሌላ ማንኛውም ተፅእኖ ይልቅ ከህዝብ ይሁንታ በመነጨ ስለሚመለከት ነው የሚል እምነት አለው፡፡ ይሁን እንጂ ዴሞክራሲን ለመገንባት እጅግ አስፈላጊ የሆነው የወንድማማችነት እሴት ደካማ መሆን የዴሞክራሲ ግንባታችንን በእጅጉ እየተፈታተነው እንደሆነም ያሳምርበታል፡፡   ከዚህ ችግር ለመውጣት የሲቪክ ባህልን በማዳበር ከአድማሰ ጠባብ ማህበረሰባዊ የጥቅም ፉክክሮች መላቀቅ የሚችል "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ" ያስፈልጋል ብሎ ያምናል መደመር፡፡ እዚህ ጋር ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ የሚባል አለ ወይ፤ ካለስ ምን አይነት ነው የሚል ነው፡፡ መደመር ለዚህ መልስ ሲሰጥ "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ፣ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ እንዲሁም የሄድንበትን መንገድ በሚገባ በመፈተሽ በእኛ ልክና መጠን በጥንቃቄ የምንገነባው ነው" ይለናል፡፡   ቀጥተኛ ዲሞክራሲ፣ የውክልና ዲሞክራሲና የመግባባት ዲሞክራሲን በዲሞክራሲ ግንባታ አማራጭነታቸው የሚተነትነው መጽሀፉ ለአገራችን የሚያስፈልገው ዲሞክሲያዊ ስርዓት "የሰው ልጆችን ተደማሪ ፍላጎት ያገናዘበ" መሆን አለበት ይላል፡፡ ተደማ ፍላጎቶችን ሁሉ እንዴት በአንዴ ማሟት ይቻል? የሰው ልጅ አቅምስ ውስን አይደለም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ እንደሚችሉ በመገመትም፤ በመደመር ዕሳቤ መሰረት የሰው ልጅ እጣ ፋንታውን የመለየት እምቅ አቅምና ነፃ ፍቃድ ያለው ፍጥረት በመሆኑ ይህንን አቅም ያለብክነት አጠራቅሞ ውጤታማ ለማድረግ በመደመር ፍኖት የመጓዝን አስፈላጊነት ያስረዳል፡፡ ትልቁ የፖለቲካ ስብራት ከሆነው ጭቆናም ሆነ ከሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮች ለመላቀቅ ማህበረሰባዊ ብሄርተኝነተን እና ሲቪክ ብሄርተኝነትን አመቻምቾ የሚጓዝ፣ ባለው የመግባባት ዴሞክራሲ ላይ ጎደለውን የልሂቃን ትብብር ለማምጣት የሚሰራ ዲሞክራሲን በአማራጭነት እንደሚከተልም በመጽሀፉ ተመልክቷል፡፡ የመጨረሻ ግቡ ደግሞ "የሲቪክ ባህል የዳበረበትና በሀሳብ ውድድር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ነው፡፡"                                የአገረ መንግስት ቅቡልነት ፈተና በአገረ መንግስት ቅቡልነት (ህዝብና ልሂቃን ሀገር መንግስቱን የፍላጎታቸው አስፈፃሚ ወኪል አድርገው የሚቆጥሩበትን መጠን) ረገድ ብዙ የቤት ስራዎች መኖራቸውን የሚጠቁመው መደመር ችግሩ ከቁስ ተሸጋሪ እሴቶች አለመዳበር እና ከአገረ መንግስት ምስታ ታሪክ ምስቅልቅሎሽ የሚመነጭ እንደሆነ ያትታል፡፡ የኢትዮጵያ አገረ መንግስት ምስረታ ከሰሜን ወደ ደቡብ በተደረገ ባህላዊ የግዛት መስፋፋት እንደመጣ በመጥቀስ አገሪቱ የተመሰረተችበት ሁኔታና ከእርሱ ጋር ተያይዞ የመጣው ለዓመታት የተገነባው የማንነት ፖለቲካ፤ ህዝቡ ለአገረ መንግስት ያለው አስተሳሰብ አሉታዊ እንዲሆንና የአገረ መንግስቱ ቅቡልነት እንዲሸረሸር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብሎ ያምናል፡፡ በዚህም ምክንያት በአገራችን ህዝቦች ዘንድ የጋራ ማንነት እና እሴት እየተሸረሸረ በመምጣቱ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይም ተጻራሪ አቋም እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን በማሳያነት ያነሳል፡፡ የኢትዮጵያን ብሄሮች በጋራ የሚያቆይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሀሳብና መርሃ ግብር እየተመናመነ መጥቶ አገሪቷ እንዳትሰነጣጠቅና ህዝቦቿም ማባሪያ ወደሌለው እልቂት እንዳያመሩ ስጋት መፈጠሩን በአጽንኦት የሚመለከተው መደመር በማህበረሰባዊ ብሄርተኞችና በሲቪክ ብሄርተኞች መካከል በእልህ የተሞላና እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው በሚል መንፈስ የሚመራውን ዋልታ ረገጥ የፖለቲካ ጉዞ ለዚህ ችግር በዋነኛ ምክንያትነት ይጠቅሰዋል፡፡ መድሃኒቱ ደግሞ ዕርቀ ሰላምና ብሄራዊ መግባባትን በማስፈን የአገረ መንግስትን ቅቡልነትን ማሳደግ እንደሚገባ ያትታል፡፡ ተቋማት አገረ መንግስቱን ሳይሆን መንግስትን ብቻ እንዲያገለግሉ ተደርገው መቀረጻቸውና ገለልተኛነታቸውን እንዲያጡ መደረጋቸውም ሌላው የአገረ መንግስቱ ቅቡልነት ፈተና እንደሆነ ያምናል፡- መደመር፡፡ ያሉትም ተቋማት "በቤተ ዘድ መረብ /ፖትሪምኒያሊዝም/ እና በተቋማዊ ችኮነት" የታጠሩ በመሆኑ የመልካም አስተዳደር እጦት የሰፈነበት ስርአት እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር ለአገረ መንግስት ቅቡልነት ፈተና ሆነዋል ባይ ነው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ለመላቀቅ፣ አስቀድሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ተንትኖና ተንብዮ የሚሰራ ቀድሞ የነቃ አመራር፣ ቢሮክራሲና ባለሙያ ማጠናከር እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ በአጠቃላይ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር ለመፍጠር የተቋማት ግንባታ የሪፎርም ስራዎች፣ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ባህል ግንባታ፣ የዴሞክራሲ ዕሴቶችን በየደረጃው ማስረጽ እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡                                 ኢኮኖሚ ከፍታ ገዝጋዦች መደመር በኢኮኖሚ እይታው እሰከአሁን ለተመዘገቡ ውጤቶች እውቅና ይሳጣል። የኢኮኖሚውን ከፍታ ሲገዘግዙ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችንም በአንክሮ ይመለከታል። የኢኮኖሚ እድገቱ ዐብይ ችግር የጥራት ጉድለት መሆኑን ይጠቁማል፡፡ እድቱ ባለፉት ዓመታት ለታየበት የጥራት ችግር አስረጅ ያላቸውን ምልክቶች ሲዘረዝርም የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ የቁጠባና ኢንቨስትመንት ፍላጐት አለመጣጣም፣ የመንግስት ፕሮጀክቶች ዝርክርክነት፣ የወጪ ንግድ መዳከምና የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የበጀት ጉድለት፣ የመዋቅራዊ ሽግግር አድካሚነት ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን ይጠቅሳል፡፡   የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ችግር እና የማክሮ ኢክኖሚ መዛባት የኢክኖሚ ስብራቱ አብይት ምልክቶች መሆናቸውን ይነሳል፡፡ በተጨማሪም የገበያ ጉድለት፣ የመንግስት ጉድለት፣ የስርአት ጉድለት፣ ለኢኮኖሚ ስርአቱ ስብራት አበይት ምክንያቶች መሆናቸውን በስፋት ይተነትናል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት መጠነ ሰፊ እድገት መመዝገቡን በአህዛዊ መረጃዎች በመተንተን የሚያስረዳው መደመር፤ እድገቱ ግን የጥራት ችግር እንዳለበት ይጠቁማል፡፡ ጥራት ያለው እድገት የተረጋጋና ዘላቂ ሆኖ ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ አስተማማኝ የስራ ዕድል የሚፈጥር፣ ድህነትን የሚያጠፋና የተሻለ የኑሮ ሁኔታ የሚያመጣ ነው፡፡ በተቃራኒው በተስተካከለ ቅኝት ውስጥ የማይፈጸሙ የእድገት አይነቶች ቀጣይነት የሌላቸው፣ ቦግ እልም የሚሉ እና የህዝቦችን የልማት ጥም የማያረኩ መሆናቸውን ያትታል፡፡   በዛለቂነት የሰው ሃይልን፣ ታሪክንና ባህላዊ ቅርስን፣ የተፈጥሮ ሀብትን መጠቀም ለኢኮኖሚው እድገት መሰረት እንደሚሆን ያስቀምጣል። ብዝሃ ዘርፎች የተዋቀረ ኢኮኖሚን፣ እውቀት መር ኢኮኖሚ መገንባትን፣ የልማት ፋይናንስ ሞዴል መቀየርን፣ የኢንቨስትመንት ኢኮኖሚን፣ የወጪ ንግድ ቀዳሚ ሆኖ የገቢ እቃዎችን ከማስቀረት ጋር መመልከትን እንዲፈትሽ ይጋብዛል፡፡ የመደመርና የውጭ ግንኙነት ዕይታ   የውጭ ግንኙነት የሰው ልጅን ተፈጥሮ ለፋክክር ወይም ለትስስር ከመበየን ጋር በጥብቅ የተቆራጥ መሆኑን የሚሰምርበት መደመር ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን ከአገራዊ አንድምታቻው ጋር እያስተሳሰሩ መተንተን ለትብብርም ሆነ ለፉክክር ወሳኝነት አለው ይለናል፡፡ የመደመር የውጭ ግንኙነት አካሄድ የዓለም አቀፍ ግንኙነት የሀይልና የተዋረድ መዋቅር ከፍተኛ ለውጥ እና ነውጥ እየተስተዋለበት መሆኑን በመጥቀስ የጂኦ ፖለቲካ ቀጠናዎች የሀይል አሰላለፍ ተለዋዋጭና ፈጣን መሆኑንም ያስረዳል፡፡ በዓለማችን የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ለውጦች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በአገራችን ብሔራዊ ጥቅምና ህልውና ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ የሚያስከትል በመሆኑ በጥንቃቄና በጥልቀት መተንተን እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ይህም አስፈላጊውን የውጭ ግንኙነት ስልት ለመተለም እንደሚያስችል ያስረዳል፡፡   ኢትዮጵያ የአቅም ክምችት ከፈጠረችባቸው መስኮች አንዱና ትልቁ የውጭ ግንኙነትና የደፕሎማሲ መስክ መሆኑን የሚመሰክረው መደመር ቀደም ባሉት መሪዎች እየተሰራ የመጣው መልካም የውጭ ግንኙነት ስራ አሁን ለምንከተለው የውጭ ግንኙነት አካሄደ ትልቅ ወረት ሊሆን እንደሚችልም ያትታል፡፡ ኢትዮጵያ በመንግስታት መቀያየር ውስጥ ክብሯን ካልነኩ በስተቀር ለትስስርና ለመግባባት ዝግጁ ሆና ቆይታለች፡፡ በዚህም ምክንያት የውጭ ግንኙነታችን ሰርክ አዲስ የሆነ የብክነት ታሪክ ሳይሆን መደመር የታከለበት የክምችት ውርስ ይዞ ቀጥሏል ይለናል መደመር፡፡   በአገራችን የውጭ ግንኙት ዙሪያ የሚደረጉ ጽንሰ ሀሳባዊ ክርክሮች በሁለት ብያኔዎች ላይ ያተካሩ ሆነው መቆየታቸውን በማንሳት አነዚህም “አውናዊነት/ ጥቅመኝነት” እና “ሀሳባዊ” ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ፍክክርን መሠረት ያደረግ ሲሆን ሁለተኛው በትብብር ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ፍክክርና ትስስርና አስታርቆ እንደሚጓዝ በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ እስከ ዛሬ በታሪካችን በተጓዝንባቸው መንገዶች በተገባነው ስም ላይ ተጨማሪ ስኬቶችን በማከልና ክምችታችንን በማሳደግ ላይ እንደሚመሰረትም በመጽሀፉ ተብራርቷል፡፡   የመደመር የውጭ ግንኙት ዕሳቤ ጥቅምን ሳይሆን ግንኙነትን ያስቀደመና "ችግሮችን ለመፍታት ቀዳሚነው ነገር ግነኙነትን ማደስ ነው" ብሎ የሚያምን ነው፡፡ በውጭ ግንኙነታችን ውስጥ "ቋሚ ወዳጅና ቋሚ ጠላት የለም" ከሚለው መርህ ይልቅ "ወዳጅና ጠላት ብሎ ነገር የለም" የሚል መርህ እንደሚከተል ይገልጻል፡፡ የመደመር የውጭ ግንኙነት ዕይታ ጎረቤት አገሮችን ማስቀደም፣ ብሔራዊ ክብርን ከፍ ማድረግ፡ የተሰሚነት ምንጭን ማስፋት፣ ገር ሀይልን በስፋት መጠቀም እና የከፍተኛ መሪዎችን የዲፕሎማሲ አማራጭ የትኩረት መስኮቼ ናቸው ይላል፡፡ ግንኙነቱ በትብብርና ፉክክር ሚዛን ላይ እንደሚያተኩርም በመጽሀፉ በስፋት ተዳሷል፡፡                                     መውጫ   ኢትዮጵያ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አዲስ ምዕራፍ የመጀመር ወርቃማ እድሎች ብታገኝም በወጉ ሳንጠቀምባቸው ባክነው ቀርተዋል የሚሉት የመደመር ደራሲ አሁንም ሌላ እድል ከፊታተን መቅረቡን ይነግሩናል፡፡ አስከትለው ግን "ይህን ዕድል በከንቱ እናባክነዋለን ወይስ ካለፈው ተመረን አገርንና ትውልድን በመደመር ከፍ ወዳለ ደረጃ እናሻግርበታለን?" የመል መረር ያለ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡   ከተናጠል ጉዞና አፍስሶ ከመልቀም አዙሪት ተላቀን ወደ ከፍታ ለመውጣት የሚያስችለንን አቅም የምናገኘው አቅማችንን ደምረን ትልቅ ወርት በፍጠር ነው፡፡ ትልቅ ወረት ደግሞ ትልቅ ትርፍ ያስገኛል፤ ይህ የሚሁነው ግን ወረቱን አክብሮ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል ነው፡፡ የመደመር እሳቤ በብዙ ጉዳዮቻችን ላይ ያለንን አቅም አሟጠንና ብክነትን ቀንሰን በመጠቀም የጋራ ግቦቻችንን እውን የምናደርግበትና የአገራችንን ህልውና የምናረግግጥበት የንቃት መንገድ  በመሆኑ እንወቅበት የሚል መልእክታቸውንም ያስተላልፋሉ፤ መጽሀፉ ደራሲ፡፡ ለዚህ ደግሞ የኑሮ ጣጣን ሁሉ ለርዕተ ዓለም ሰጥቶ ያንን እየመነዘሩ ከመኖር ይልቅ መርህንና ነባራዊ ሁኔታን እያስታረቁ መኖድ የሚያስችል ዝግጁነት ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡   በአጠቃላይ የመደመር እሳቤ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ገብቶ ሁላችንም ተደምረን አገራችንን መለወጥና ህልውናችንን ማረጋገጥ እንችል ዘንድ የዕሳቤውን መሠረታዊ ሀሳቦች በየደረጃው በተለያየ መንገድ ማድረስ ያስፈልገል፡፡ ለዚህም ተጨማሪ የመደመር ሀሳቦችን ያካተተ መጽሀፍ በቀጣይ ለአንባቢ እንደሚያደርሱ ቃል ሰጥተዋል፡፡ የተበረከተልንን አንብበን ቀጣዩን እንጠብቅ!
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም