የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል የመንግስት አስፈፃሚና የምርምር ተቋማት ቅንጅት መጠናከር አለበት

59

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 26 ቀን 2012 በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የሚመጡ ጥፋቶችን ለመከላከል የመንግስት አስፈፃሚና የምርምር ተቋማት ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህዋ ሳይንስና አስትሮኖሚ ዳይሬክተር ዶክተር አታላይ አየለ ተናገሩ።

ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር "ከምድር ወለድ አደጋ ስጋት ወደ ተግባራዊ እርምጃ በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል የሁለት ቀን ውይይት እያደረገ ነው።

በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ከአሁን በፊት የደረሱና እየደረሱ ያሉ የመሬት መንሸራተት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ እሳተገሞራና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችና ቀጣይ ስጋቶች ላይ ሰፊ ሃሳቦች ተነስተዋል።

አደጋው በአብዛኛው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚመጣ መሆኑንና በቅድመ ጥናትና መከላከል ላይ ትኩረት ካልተደረገ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችልም ተነስቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህዋ ሳይንስና አስትሮኖሚ ዳይሬክተር ዶክተር አታላይ አየለ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋ የመከላከል ስራ ብዙ አልተለመደም።

እስካሁን ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንም ይሁን በሌሎች የመንግስት ተቋማት የሚሰራው ስራ ጉዳት ከደረሰ በኋላ እሳት የማጥፋትና እርዳታ የማሰባሰብ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አደጋው በሚያደርሰው የጉዳት መጠንም ይሁን በድግግሞሹ ፍጥነት እየጨመረ በመሆኑ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና አስፈፃሚነ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ዩኒቨርሲቲዎች ወይም የምርምር ተቋማት የበሰለ ጥናት ያለማቅረብ የመንግስት አስፈፃሚ ተቋማትም ቢሆኑ ምርምሮቹን ተግባር ላይ አለማካተት ችግር እንደሚታይባቸው ገልጸዋል።

የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው አስቀድሞ አደጋ መከላከል ላይ የመስራት ችግር መኖሩን ተናግረዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት በአሁኑ ወቅት ቅንጅት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፈጥሮ አደጋ ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ቦታዎችን የመለየት፣ መልማት ያለባቸውን የማልማት፣ ሰውና እንስሳ እንዳይደርስባቸው የሚከለሉትንም የመከለል ስራ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

ከአሁን በፊት በደረሱ የጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና ተያያዥ የተፈጥሮ አደጋዎች የሰው ህይወት መጥፋቱንና  ከ162 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ እነሱንም መልሶ የማቋቋም ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

''በተፈጥሮ አደጋ ከተፈናቀሉት መካከል አብዛኞቹ መልሰው ተቋቁመዋል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም