በአማራ ክልል 44 ሺህ ኩንታል ቡና የመልቀም ስራ እየተካሔደ ነው

233

ባህርዳር ኢዜአ ጥቅምት 26 ቀን 2012 በአማራ ክልል ከለማው የቡና መሬት 44 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የለቀማ ስራ እየተካሔደ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ግርማ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የቡና ልማትን በማስፋፋት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግና በአገር አቀፍ ገበያው የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ቀደም ሲል በቡና ተክል ከለማው 10 ሺህ ሄክታር መሬት የደረሰውን የቡና ምርት የመልቀም ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ከያዝነው ወር ጀምሮ ምርቱን የመልቀም ስራ የተጀመረባቸው አካባቢዎች ለቡና ምርት ተስማሚ ናቸው ተብለው በተለዩ 20 ኩታ ገጠም ቡና አብቃይ ወረዳዎች ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

በምርት ዘመኑም ከ44 ሺህ 800 ኩንታል በላይ የቡና ምርት ይሰበሰባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን እየተሰበሰበ ያለው ምርት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ14 ሺህ ኩንታል ብልጫ ይኖረዋል ።

ከሚሰበሰበው ምርትም 3 ሺህ 700 ኩንታል ንፁህ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በዕቅድ መያዙን ገልጸው ቀሪው ምርት ለአካባቢ ገበያ ለፍጆታ እንደሚውል አስረድተዋል።

አምራቹ አርሶ አደር ምርቱን በአግባቡ በመልቀም፣ በማድረቅና በማከማቸት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለገበያ ማቅረብ እንዲችልም ቢሮው በተዋረድ በሚገኙ ባለሙያዎች አማካኝነት ስለቡና ምርት አሰባሰብ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ የወይንማ አምባየ ቀበሌ አርሶ አደር ተዋበ በቃሉ በሩብ ሄክታር መሬት ካለሙት የቡና ተክል የደረሰውን ምርት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የመልቀም ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"አሁን ላይ እየሰበሰቡት ካለው ቡናም ሁለት ኩንታል ንጹህ የቡና ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ" ጠቁመው ምርቱን በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ካገኙት ሁለት ኩንታል የቡና ምርት ከራሳቸው ፍጆታ የተረፈውን ለገበያ አቅርበው በመሸጥ ከ12 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግታቸውን አውስተዋል።

በግማሽ ሄክታር መሬት በ2009 ዓ.ም የተከሉትን ቡና እየተንከባከቡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ ጃቢጠህናን ወረዳ የጎርፍቃውንቼን ቀበሌ አርሶ አደር አለሙ መሀሪ ናቸው።

የቡና ተክሉ ምርት መስጠት የሚያስችለውን ደረጃ ላይ በመድረሱ ዘንድሮ የተሻለ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል ።

ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን በክልሉ በቡና ከለማው መሬት ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም