በስርአተ ምግብ መጓደል በህጻናት ላይ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግር ለቀነስ እየተሰራ ነው

112
ጎንደር (ኢዜአ) ጥቅምት 26 ቀን 2012ዓ.ም በማዕከላዊ ጎንደር ምዕራብ በለሳ ወረዳ የአርሶ አደሩን ልማዳዊ የስርአተ ምግብ አጠቃቀም ለማሻሸል መሰራቱ  ተገለጸ፡፡ በወረዳው ከ10 ህጻናት መካከል ስድስቱ በስርአተ ምግብ አለመመጣጠን ለአካላዊና አዕምሯዊ እድገት ውሱንነት (የመቀንጨር) ጤና ችግር ተጋላጭ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ በወረዳው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጀግናው ክብሩ ለኢዜአ እንዳሉት በስርአተ ምግብ መጓደል በህጻናት ላይ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግር ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። ለእዚህም በወረዳው አርባያ ቀበሌ ከመንግስት በተሰጠ 20 ሄክታር መሬት ላይ ሞዴል የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡ ሞዴል የመስኖ ፕሮጀክቱ አትክልትና ፍራፍሬ አልምቶ በማሰራጨት ህጻናት፣ አጥቢ እና ነፍሰጡር እናቶች የተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀትና የአመጋጋብ ባህል እንዲያጎለብቱ እገዛ እንደሚያደርግ አመልክተዋል። በተጨማሪም ከመስኖ ፕሮጀክቱ የሚለቀቀውን የመስኖ ውሃ በመጠቀም 131 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በ60 ሄክታር መሬታቸው ላይ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ምርቱን ለቤት ውስጥ ፍጆታ ብቻ የሚያውሉበት አሰራር እንደሚመቻች አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡ አቶ ጀግናው እንዳሉት ፕሮጀክቱ አርሶ አደሮቹ በተለይ እንደ ጎመን፣ ካሮት፣ ቀይ ስር፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያና ድንች የመሳሳሉትን የጓሮ አትክትልቶች በዓመት ሦስት ጊዜ በመስኖ አልምተው ልጆችንና ነፍሰጡር እናቶችን የስርአተ ምግብ ተጠቃሚ የሚያደርጉበት ነው፡፡ በተጨማሪም ቋሚ የፍራፍሬ ችግኞችን ለአርሶ አደሮቹ በማሰራጨት አቦካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያና ሌሎች ፍራፍሬዎችን አልምተው ለቤት ውስጥ ፍጆታ በማዋል ጤናማ የአመጋጋብ ባህል እንዲተገብሩ የሚያደርግ መሆኑን ነው የገለጹት። ባለፈው ዓመት ግንባታው የተጀመረው ሞዴል የመስኖ ፕሮጀክቱ በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በመጪው የካቲት ወር ሥራ እንደሚጀምር ተመልክቷል፡፡ "በመስኖ ግንባታው አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመስኖ ውሃ ማስተላላፊያ የካናል ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል" ያሉት አስተባባሪው፣ ዋናው የመስኖ ግንባታና የውሃ ፓንፕ ተከላ ሥራም በመፋጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በስርአተ ምግብ አጠቃቀም ጉድለት በወረዳው የሚታየውን ከ10 ህጻናት መካካል 6ቱ የሚደርስባቸው የመቀንጨር ጤና እክል በመለወጥ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡ "የምናመርተውን አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንቁላል፣ ዶሮና ቅቤ ገበያ እውጥቶ ከመሸጥ ውጪ በቤት ውስጥ ልጆችና ነፍሰጡሮች እንዲመገቡ የማድረግ ባህላችን ዝቅተኛ ነው" ያሉት ደግሞ በወረዳው የአርባያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ባይለየኝ ደርሶ ናቸው፡፡ የመስኖ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ሞዴል በመሆኑ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ልጆቻቸውንና ነፍሰ ጡር እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ከበቡሽ ሞላ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ነፍሰ ጡሮችና ሁለት ዓመት ያልሞላቸው ህጻናት ሊመገቡ የሚገባቸውን የምግብ አይነቶች ለማዘጋጀት የሚያስችል እውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ከሚኖረው 200ሺህ ህዝብ መካካል 60 በመቶው የሚሆነው በልማዳዊ ስርአተ ምግብ አጠቃቀም ለመቀንጨር የጤና ችግር ተጋላጭ መሆኑን ከፕሮግራሙ አስተባባሪ መግለጫ ለማወቅ ተችሏል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም