የጋዜጠኞች የጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ ሚዲያዎች 'በሕግ ይጠየቁ' ጥያቄዎችና የብሮድካስት ባለስልጣን አቋም

117
ኢዜአ ጥቅምት 26/2012 ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል መገናኛ ብዙኃኑ የራሳቸውን አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል ይላሉ - ኢዜአ ያነጋገራቸው ጋዜጠኞች። አንጋፋው ጋዜጠኞ ጥበቡ በለጠ የኢትዮጵያ ሚዲያ ብዙ ችግሮች የነበሩበት፣ አገሪቷም ለዓመታት በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች 'የጋዜጠኞች ቀበኛ' ተደርጋ ስትጠቀስ የቆየችበት መሆኑን ያወሳል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንጻራዊ ነጻነት መፈጠሩን ገልጾ፤ ዳሩ ግን በተለይ በመንግስት በጀት የሚንቀሳቀሱ የክልል ሚዲያዎችና በግለሰቦች የተቋቋሙ የአንድ ወገን አስተሳሰብ ማራመጃ ሚዲያዎች መበርከታቸውን ይናገራል። ሌላው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ጌትነትም በርካታ መገናኛ ብዙኃን አንድን ማኅበረሰብ ለጥቃት የሚያጋልጡ የጥላቻና የቡድን ፕሮፓጋንዳ ተቋማት ሆነዋል ባይ ነው። እንደ ጋዜጠኞቹ እምነት በየጊዜው እንደ ቀላል እየታዩ ለእርስ በእርስ ግጭት የሚቀሰቅሱ ሚዲያዎች ከባድ ዋጋ እያስከፈሉ ነው። እናም ከህዝብ ነጻ አስተሳሰብ ይልቅ የአንድ ወገን ፖለቲካዊ አስተሳሰብን የሚያራምዱ አክራሪ መገናኛ ብዙሃን ላይ ለአገርና ለሕዝብ ደህንነት ሲባል የሕግ ተጠያቂነት ማስፈን እንደሚገባ ገልጸዋል። ችግሩን ያቃልለዋል የተባለው አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅም በፍጥነት መፅደቅና መተግበር ይገባዋል ሲሉም ጠይቀዋል። የሚዲያ ባለሙያዎችም ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ተላቀው በስራዎቻቸው የሚደርሰውን የመጨረሻ ውጤት በማመዛዘን ሙያዊ ኃላፊነቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መክረዋል። በሕግ ተጠያቂነት ረገድ ጋዜጠኛው ብቻ ሳይሆን ተቋሙም መጠየቅ እንዳለበት አሳስበዋል። በሌላ በኩል ቀደም ሲል ለፕሬስ ነጻነትና ለጋዜጠኝነት ሙያ ሳንካ በሆኑ አንቀጾች አሁንም ጋዜጠኞች መከሰስና መታሰር እንደሌለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ለመገናኛ ብዙሃን ፈቃድ ከመስጠት እስከ ማገድ ስልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከሰሞኑ የሩብ ዓመት ሪፖርቱን ለሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ መስመር የሳቱ ሚዲያዎችን መስመር ለማስገባት በአዋጅ የተሰጠውን ሃላፊነት አልተወጣም የሚል ወቀሳ ደርሶበታል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ግን በጎ የሚሰሩትን ማበረታታት እንዳለ ሁሉ በህዝቦች መካከል ጥላቻን የሚዘሩ፣ ግጭት የሚቀሰቅሱና የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ቅጥ ያጡ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል። ባለስልጣኑ እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክር ለማስፈራራት የሚሞክሩ ወገኖች እንዳሉ ገልጸው፤ ወገንተኛ እንዳይመስል፣ ፖለቲካዊ አረዳድ እንዳይኖር፣ ጥንቃቄ በተሞላበትና በሆደ ሰፊነት እንዲሁም በሳይንሳዊ መንገድ አጥንቶ ተጠያቂ ለማድረግ እንደዘገየ ተናግረዋል። የተለያዩ ሚዲያዎች ከጋዜጠኝነት ይልቅ በፖለቲካ አክቲቪዝም ላይ መጠመዳቸውን ገልጸው፤ ከህግ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት በሕጉ ድንጋጌ መሰረት ጣቢያ እስከመዘጋት ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የባለስልጣኑን ኃላፊነትም ሆነ የሚዲያ ተጠያቂነትን ያሰፍናል የተባለውና የተሻሻለው የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ገልጸዋል። በረቂቅ አዋጁ ቀድሞ የብሮድካስት አዋጅ የሚለው ሕግ የሕትመትና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በማካተት 'የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ' በሚል የቀረበ ሲሆን ባለስልጣኑም 'የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን' እንደሚሰኝ ተደንግጓል። የአገሪቷ ሚዲያ የሚመራበት የራሱ ፖሊሲ መቀረጹን በመግለጽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅና ፖሊሲውን በመናበብ ጎን ለጎን እንዲጸድቁ ባለስልጣኑ ጥረት እያደረገ መሆኑን ዶክተር ጌታቸው ጠቅሰዋል። ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎቹ ከሁለት ወራት በኋላ ለምክር ቤቱ ቀርበው እንደሚጸድቁም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም