ግብፅ ከሱዳን ጋር የሚያገናኛትን 6 ሺ ኪሎ ሜትር እርዝመት ያለው የባቡር መንገድ ልትገነባ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ ከሱዳን ጋር የሚያገናኛትን 6 ሺ ኪሎ ሜትር እርዝመት ያለው የባቡር መንገድ ልትገነባ ነው ተባለ
71
ኢዜአ ጥቅምት 26/2012 ግብፅ ከሱዳን ጋር የሚያገናኛትን ስድስት ሺ ኪሎ ሜትር የባቡር መንገድ ልትገነባ መሆኗን በትራንስፖርት ሚኒስትሯ ካሚል ኢል-ዋዚር በኩል አስታውቃለች ሲል ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል፡፡ ፕሮጀክቱ በግብፅ ደቡባዊ ክፍል ከሚገኘው አቡ ሲምበል ከተሰኘ አካባቢ የሚጀመር ሆኖ አቡ ሃማድ ወደተሰኘች የሱዳን አካባቢ የሚወስድ መንገድ መሆኑንም ዘገባው አመላክቷል፡፡ የባቡር መንገዱ ሲጠናቀቅም የሁለቱን ሃገራት የሸቀጣሸቀጦች እንቅስቃሴና የሰዎችን ዝውውር ለማሳለጥና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንደሚያስችል ዘገባው አትቷል። ይህ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት የተቀረፀው በሁለቱም ሃገራት የትብብር ኮሚቴዎች መሆኑን ያመላከተው ዘገባው የትብብር ኮሚቴው በፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ እና በቀድሞ የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ይመራ እንደነበርም አስታውሷል፡፡ በሁለቱ ሃገራት መካከል በርከት ያሉ የትብብር ማዕቀፎች መኖራቸውን የጠቆመው ሚዲል ኢት ሞኒተር ይህ ፕሮጀክትም አንዱ የትብብራቸው አካል መሆኑን አስታውቋል፡፡ አዲሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በተመረጡ ከሰዓታት በኋላ በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳሚ ሻኩሪ የተመራ ልዑካን ቡድን ሱዳንን መጎብኘቱን ዘገባው አውስቷል፡፡ ካይሮ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ውዝግብ የካርቱን ድጋፍ በቋሚነት በመሻት በርካታ ሙከራዎችን እያደረገች መሆኗንም ዘገባው ያሳያል፡፡