በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተከሰተው ድርቅ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደረስ ርብርብ እንዲደረግ ተጠየቀ

74
ሰቆጣ (ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2012ዓ.ም በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የተከሰተው ድርቅ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አፈ ጉባዔ ጥሪ አቀረቡ። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 7ኛ ዓመት አራተኛ አስቸኳይ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል። የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኃይሉ ሚሰው ጉባኤውን በንግግር በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተመጣጠነ ዝናብ አለመጣሉ ድርቅ እንዲከሰት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። በዚህም በአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት የእለት ደራሽ ምግብ፣ እህልና ሌሎች ድጋፎች እየቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ርብርብ እንዲያደርጉና የምክር ቤት አባላትም ተባባሪ እንዲሆኑ አቶ ኃይሉ ጥሪ አቀርበዋል። ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ በርካታ ዜጎች የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት መዘረፍና ውድመት እንደገጠማቸውም አስታውሰዋል። "ማንነትንና ሃይማኖትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ጥያቄዎች በጸረ ዴሞክራሲ አካሄድ ስለሚከናወኑ ኢ-ሰብዓዊ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆነዋል" ሲሉም ገልጸዋል። አፈጉባኤው እንዳሉት በብሔረሰብ አስተዳደሩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም በሚሉ ምክንያቶች መንገድ መዝጋት፣ የመንግስትን ተልዕኮና አቅጣጫዎች አለመቀበል ችግሮች ተስተውለዋል። በተጨማሪም በአንዳንድ ወረዳዎች ህዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ የመከልከል ሥራ ሲሰራ እንደነበር ነው ያስታወሱት። "በመሆኑም በቀጣይ በህገወጥ መንገድ አስገድዶ ለማስፈፀም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በእንጭጩ ልንታገላቸው እና ልናስተካክላቸው ይገባል’’ ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱ በአንድ ቀን አስቸኳይ ጉባዔው የብሔረሰብ አስተዳደሩን የየተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን የ2012 በጀት ዓመት እቅድ መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን በተጓደሉ አመራሮች ምትክ ሹመት ሰጥቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም