ግብረ ገብነትን በተግባር

1245

በቁምልኝ አያሌው እና ቀበኔሳ ገቢሳ ( ኢዜአ)

በተለምዷዊው ሀገረኛ አነጋገር “የተማረ ይግደለኝ” ሲባል ብዙ ጊዜ ይሰማል። ልጅ እያለን ትርጉሙ ሳይገባን “ሰው ለመግደል ደግሞ ምሁር መሆን ያስፈልጋል እንዴ? ሽፍታ መሆን ብቻ በቂ አይደለምን?” የሚል አመለካከት ነበረን። በኋላ ግን እየዋለ እያደረ እኛም እያደግን እየበስልን ስንመጣ አባባሉ ሳይንሳዊና ሚስጥር አዘል መሆኑን ተረዳን።

ከትርጉሙ መነሻ ሀሳብ ስንነሳ “የተማረ ይግደለኝ” በጀምላ ፊደል ለቆጠሩ ሁሉ ሳይሆን በእውቀት፣ በምክንያትና በእውነታ ላይ የተመሰረተ ስብዕና፣ አርቆ አሳቢነት፣ አስተዋይነት፣ ሚዛናዊነት፣ ፍትህዊነት፣ ህዝባዊ ወገንተኝነትንና የሰብዓዊ ርህራሄ መገለጫ ለሆናቸው  ምሁራን ሁሉ የሚሰጥ የምስጋናና የአድናቆት መግለጫ መሆኑን የትምህርት ፍልስፍና ያስረዳናል።

በሌላ አነጋገር ችግርን ለመፍታት ዕውቀት፣ ትዕግስት፣ ጥበብ፣ ብልህነት እና ቆራጥነትን በተላበሰ አካሄድ ለሕብረተሰቡ የሚያበረክቱትን ስራን የሚያመላክት አባባል ነው። በሰው ልጆች ታሪክ ብዙ ጠቢባንና ልሂቃን በጊዜያቸው ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ብዙ አስገራሚ እና አስደናቂ የሆኑ ዘመን ተሻጋር ስራ ሰርተው አልፈዋል።

እነዚህ ግለሰቦች በህዝቦች የለውጥ ጎዳና ላይ እዚህ ግባ የሚባል ነገር ባያበረክቱም እንኳን ሂደቱን የማቀላጠፍ ወይም የማዘግየት ሚና ይጫወታሉ። በመግቢያው ላይ እንዳስቀመጥነው የተማረ ይግደለኝ የሚለው አገረኛ አባባል ትልቅ መልዕክት አለው። ምክንያቱም ክፉም ሆነ ደግ በተማረ ያምራል። እዚህ ላይ ግን አንድ አከራካሪ ነገር አለ። የተማረ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው ሃሳብ የሚሰጠውን ትርጓሜ ማለት ነው፡፡ የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ምሁር” ወይም የተማረ ሰው የሚለውን ቃል “በትምህርት በዕውቀት የበሰለ አዕምሮ ያለው ሰው” እንደሆነ ይጠቅሳል። በዚህ መሰረት ምሁር ሲባል በትምህርት እና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ወይም ማህበራዊ ግንኙነት  ዕውቀት በመቅሰም ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ በማየት ማገናዘብ የሚችል ሰው ምሁር እንደሚባል ያስቀምጣል።

በመሰረቱ የተማረ ሰው ለመሆን መደበኛ እና ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ መማር ያስፈልጋል፤ በትምህርትም ዕውቀት ይገኛል። በዚህም ብዙ የተማረ ሰው ሊኖር ይችላል፤ ብዙ ነገር የሚያውቁ ሰዎች ይኖራሉ።

በትምህርት የሚገኘው ዕውቀት በተግባር ለውጥና መሻሻል ካላመጣ ትምህርት መማሩና ማስተማሩ በራሱ ትርጉም የለውም። የአንድ ሰው በትምህርት የተገኘ ዕውቀት ፋይዳ የሚኖረው በራስና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ሲያስችል ብቻ ነው።

አንድ ሰው “የተማረ”  የሚባለው በትምህርት ከሚገኝ እውቀት ብቻ  ሳይሆን የህብረተሰብን  አኗኗር ለመቀየር፣ የዜጎችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ለማሻሻል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው ። የተማረ ሰው የሰዎችን ኑሮና አኗኗር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት አለበት፡፡ በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆንም አለበት።

ይህ ለሌሎች ሰዎች ሲባል የሚደረግ አይደለም፤ ከዚያ ይልቅ  በሰዎች ሕይወት እሴት የማይጨምር ነገር ለራሳችንም ሆነ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ፋይዳ-ቢስ ተደርጎ ስለሚወሰድ ዘለቄታና እርካታ አይኖረውም። ስለዚህ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል የሚያበቃው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ዘዴ ሆኖ ከተገኘ ነው፡፡ ይኸው ምሁርነት የተሰኘው ማዕረግና ክብርም ከዚህ አንፃር ታይቶ፣ ተመዝኖ እና ተቃኝቶ የሚሰጥ ፀጋ ነው።

በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የተጠናው ጥናት እንደሚያመለክተው  ይሰጡ በነበሩት የትምህርት ዓይነቶች ውስጥም ሰብዓዊ መብት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነት የመሳሰሉ ሃሳቦች የተካተቱበት እንዳልነበር በመግለፅ በሁለቱም መንግሥታት የነበረው የሥነ ምግባር ትምህርት የርዕዮተ ዓለም ትምህርት እንጂ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ የሥነ ምግባር ትምህርት አልነበሩም ሲል ያትታል። በዚህ መሰረት ትውልድን ስለ መብትና ግዴታ ለማስተማር በትምህርት ፖሊሲ ተካቶ የስነ ዜጋ ምግባር ትምህርት ተቀርጾ መሰጠት ከጀመረ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሆኖታል።

ይሁን እንጂ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነፅ ረገድ ውጤታማ እንዳልሆነ ጥናቱ ከነ ምክንያቶቹ ነቅሶ ያሳያል። የዴሞክራሲ በተግባር አለመኖር፣ የባለሙያዎች እጥረት፣ ለትምህርቱ ያለው አመለካከት፣ የትምህርቱ ይዘት እና ሌሎች ተግዳሮቶች ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።በመሆኑም ይህም እንደ ቀደመው ዘመን ርዕዮተ ዓለምን የማስረፅ እንጂ ተማሪዎችን በሥነ ምግባርና በሞራል አንፆ ማውጣት የሚያስችል አይደለም የሚል ትችት የሚስተናገድበት ሆኗል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፍልስፍና ምሁር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋም የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት(ሲቪክ ኤዱኬሽን) ትምህርት መልካም ቢሆንም ግብረ ገብነትን ሊተካው አይችልም ሲሉ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት በሚሞግት አስተያየት ቆመዋል። ዶክተሩ አክለውም "የግብረ ገብ ትምህርት ድሮ ልጅ እያለን ከሁለተኛ ክፍል ወይም ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ እንማር ነበር ፤ በመሆኑም ተመልሶ መሰጠት አለበት " ሲሉ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ይደግፉታል።

‹‹እንዴትና ምን መማር እንዳለበት የሚያውቅ፣ ነጻ ሆኖ የሚያስብ፣ ለነገሮች ትክክለኛ ብያኔ የሚሰጥ እና የሚጠበቅበትን ለመሥራት ራሱን በራሱ የሚቀሰቅስ ነው።›› በማለት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የአዲሱን ዓመት የከፍተኛ ትምህርት መጀመርን አስመልክተው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጥቅምት 03, 2011 ዓ.ም ባስተላለፉት መልዕክታቸው አስረድተዋል።

በጥቅሉ የተማረ ሰው ማለት ከሌሎች ጋር ሲኖር ልዩነቶችን በሠለጠነና ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ ለመፍታት የሚችል፣ ችግሮችን በመጠናቸው ልክ የሚረዳና መፍትሔ የሚያፈላልግ፣ የራሱን ስሜትና ጸባይ እንዴት ማስተዳደር እንደሚችል የሚያውቅ፣ የሥራና የኑሮ ሥነ ምግባር ያለው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።  በትምህርት ስርዓት ውስጥ መማር ክፉውን ከደጉ ለይቶ ለማወቅ፣ መልካም ስራ ለመስራት፣መልካም ለመሆንና  አብሮ ለመኖር የሚሉት አራት ዋና ዋና ምሰሶዎችን ይይዛል።  በዚህም በመታገዝ ፆታ፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ቀለምና እድሜ ሳይለይ ለሰው ዘር ሁሉ እኩል አመለካከት ያለው፣ ከለውጥ ጋር እንዴት መሄድ እንዳለበት የሚረዳ ብቸኛው ማሰሪያ ትምህርት እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ።

ለኪነ ጥበብ፣ ለተፈጥሮ፣ ለእውቀት ልዩ ፍቅር ያለው፣ የማያውቃቸውን ባሕሎች፣ ቋንቋዎችና አካባቢዎች ለማወቅ የሚተጋ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው መናገራቸውም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በአዲሱ የትምህርት ፍኖታ ካርታ  ውስጥ የግብረ ገብ ትምህርትን ጨምሮ  ክሪቲካል ቲንኪንግ እና ሌሎችም ትውልድን ያንጻሉ ተብሎ የተገመቱ የትምህርት ዓይነቶች መካተታቸው ጥሩ ነው የሚል አቋም እንዳላቸውም ዶ/ር ዳኛቸው ይናገራሉ።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ሥነ ባህሪ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር መስከረም ለቺሳም በሃሳቡ ላይ ተቃውሞ የላቸውም። ግብረ ገብ በትምህርት ቤት ውስጥም ሆነ በከፍተኛ ተቋም ውስጥ በየትምህርት ዓይነቶቹ ውስጥ ገብቶ፣ አኗኗራችንም ውስጥ የሚገለፅ እየሆነ መሰጠት አለበት የሚል አቋም አላቸው። ግቡን እንዲመታም ከተለያየ አቅጣጫ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ይመክራሉ።

በእርግጥ የተማረ ሰው  ይህን የሚያደርገው ከግል ወይም ከተወሰነ ቡድን ጥቅም አኳያ ሳይሆን በመሰረታዊ የነፃነትና የፍትህ መርሆች ላይ ተመስርቶ ነው። የፍልስፍና ምሁሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ‘‘የተማረ ሰው ማለት ክህሎት ያለው ማለት ብቻ አይደለም፤ ከዓመት ዓመት በስልጠና ውስጥ የኖረ እና ያነበበ ሰው ማለትም አይደለም፤ ሚዛናዊ ሆኖ መጠይቅ የሚችል፣ ሁኔታዎችን ማገናዘብ የሚችል፣ ወደ ኋላ ሔዶ ታሪክ እና ስነፅሑፎችን በማንበብ ለማወቅ የተጋ እና ያወቀውን ማገናዘብ የሚችል ነው’’ በማለት ይገልፁታል።

የተማሩ ሰዎች በየትኛውም ጊዜና ቦታ የሰዎች ነፃነት ሲገፈፍ ና ፍትህ ሲዛባ በይፋ በመናገርና በመፃፍ ተቃውሟቸውን ይገልፃሉ፤ ይሟገታሉ። ነፃነትና እኩልነት ሲረጋገጥም ድጋፍና ደስታቸውን በይፋ ይገልፃሉ። እነዚህ የነፃነትን ጣዕም የሚያውቁ በሁሉም ጊዜና ቦታ ለሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት ይሟገታሉ፤ ድንቁርና ና ጭቆናን ፊት-ለፊት ይጋፈጣሉ፤ ለመላው የሰው ልጆች ነፃነትም መሟገት ይጀምራሉ።

በአጠቃላይ “ምሁራን” ወይም የተማረ ሰው ማለት ሃሳብና አስተያየታቸውን በአደባባይ በመግለፅ የህዝብን ጥያቄ የሚያንፀባርቁ እንዲሁም ኋላ-ቀር አመለካከት ና ግትር አቋምን በይፋ የሚሞግቱ አካላት ናቸው። በተጨማሪ  የትምህርት ዋና ተግባር መሆን ያለበት አንድን ሰው እንዴት በትኩረት እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሰብ እንዲችል ማድረግ እንደሆነ አጠቃላይ የትምህርት ስርዓት ሂደት ያስረዳናል።

የትምህርት ትክከለኛ ግብ የተማረ አቅም እና ምሉዕ ምግባር መፍጠር ነው። የተማሩ ሰዎች በትምህርት ዕውቀት ያገኛሉ፤ ባገኙት ዕውቀት ግለሰባዊ እና ማህበረሰባዊ ነፃነትን ይጎናፀፋሉ። በአሁን ሰዓት ሀገራችን የሚያስፋልጋት የተማረ ሰው ብቻ ሳይሆን ተምሮም በማስተዋል እና በማገናዘብ ህዝቦችን ከድህነት አረንቋ ማውጣት የሚችል አስተዋይ ሰው እና ትውልድ ነው። የተማረ ሰው  ከስሜታዊነት፣ ከግብዝነት እና ከቂም-በቀል ነፃ በሆነ ና በሰከነ አዕምሮ መገንዘብና መተንተን የሚችል እና ትምህርቱን መተርጎም በሚያስፈልግበት ቦታና ሁኔታ በመተርጎም ለሀገር መልካም ነገር የሚያበረክት ነው፡፡

የተማረ ዜጋ መፈጠሩ ለሃገር ግንባታ ብሎም እድገትና ብልፅግና ወሳኝ ጉዳይ ነው። የተማረ ሰው  የነበረን  አሮጌ አሠራርን በመቀየር ወይም በማዘመን  ለመጭው ትውልድ የተሻለና የዘመነ አሰራርን ያሰረክባል፤ ያስተላልፋል።

ነገር ግን አሁን ባለንበት ዘመን  የተማረ ሰው ነው የሚባለው አንዳንድ ሰው አልተማሩም ከሚባሉት ሰዎች አንሶ መገኘቱ ብዙዎቹን ከማሳዘኑም በላይ የትምህርት ፖሊሲ ላይ ጥያቄ እያስነሳ ነው።  የተማረ ማን ነው? መገለጫዎቹስ? ተብሎ ሲጠየቅ «እገሌ» ነው ሲባሉ ነገሩ እውነት ይሁን ሀሰት ከሰውየው ማንነት በመነሳት ይገምታሉ።

ይህን ነገር የተማረ ነው ወደ ተባለው ሰው ስናመጣው ተገልብጦ እናገኘዋለን። በአሉባልታና በወሬ አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ሲያቃቅር ይታያል። እነዚያን ምንም ተንኮል ለማያውቁት የዋህ አርሶአደሮች ተንኮል በማስተማር ዘረኝነት የሚሰብከው የተማረ የተባለው ሰው ነው። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ መማር ማለት ምን ማለት ነው የሚል ጥያቅ የሚያስነሳው።

የዛሬው ትውልድ ዛሬ ለሰራው ስራ እንጂ ትናንት አያቶቹና ቅድመ አያቶቹ ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂ መሆን ስለሌለበት የቀደሙ ጥፋቶችን የማከምና መልካም ስራዎችን አጉልቶ የመዘከር ኃላፊነት በዚሁ አሻጋሪ ትውልድ ጫንቃ ላይ የወደቀ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ በየቦታው እየሄዱ ፈሰስ መቅደድ ፍሜው መሬቱን በጎርፍ ማስበላት እደሆነም ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ለሀገራችን ሁለንተናዊ ለውጥ እና እድገት አስተዋፅኦ የሚያበረክት እና በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ትምህርት ወሳኝ እና ቁልፍ መሳሪያ ስለሆነ በትምህርት ማሻሻያ ስርዓታችን ላይ የግብረ ገብ ትምህርት በተግባር ትኩረት ተሰቶት ሊካተት ይግባል። በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን የሚያስፋልጋት የተማረ ሰው ብቻ ሳይሆን ተምሮም በማስተዋል እና በማገናዘብ ህዝቦችን ከድህነት አረንቋ ማውጣት የሚችል አስተዋይ እና ምክንያታዊ ትውልድ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም