የአንበጣ መንጋው ከ4ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት አደረሰ

62
(ኢዜአ) ጥቅምት 25 /  2012 በደቡብ ወሎ ዞን የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ የደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። ሕብረተሰቡ የአንበጣ መንጋውን በባህላዊ መንገድ ከመከላከል ጎን ጎን የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑ ተመልክቷል። የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋ በየጊዜው ከአፋር ክልል ወደዞኑ የሚገባ በመሆኑ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤት እንዳያመጣ አድርጎታል፡፡ "የመልክዓ ምድሩ አቀማመጡ አስቸጋሪ በመሆኑ በአውሮፕላን ኬሚካል ለመርጨት አልቻልንም" ያሉት ምክትል ኃላፊው በባህላዊ መንገድ ብቻ የሚደረገው የመከላከል ስራ ከአንበጣው በፍጥነት መዛመት ባህሪ ጋር ተያይዞ ለውጥ አለማምጣቱን ተናግረዋል። እስካሁንም በቃሉ፣ ወረባቦና አርጎባ ወረዳዎች ባሉ11 ቀበሌዎች ላይ ብቻ የነበረው የአንበጣ መንጋ ሳምንት ባለሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ 25 ቀበሌዎች በመስፋፋት ከ4 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት በለማ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ አቶ አሊ እንዳሉት የአንበጣ መንጋው በዋናነት እየተጎዳ ያለው ቆላ አካባቢ የተዘራ የማሽላ ሰብል ሲሆን እስካሁን አንበጣው በሰፈረባቸው አካባቢዎች ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሰብል ወድሟል። "ቀሪው ሙሉ በሙሉ እንዳይወድምና አርሶ አደሩ ከምርት ውጭ እንዳይሆን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ በየወረዳው ያሉ ተማሪዎችና ህብረተሰቡን በማተባበር አንበጣውን ከመከላከል ሥራ ጎን ለጎን የደረሱ ሰብሎች እየተሰበሰቡ ነው" ብለዋል፡፡ የአንበጣ መንጋው ያለተከሰተባቸው ወረዳዎችም ተማሪና የግብርና ባለሙያን አስተባብረው አንበጣው ወደተከሰተበት አካባቢ እያላኩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከአንበጣ መከላከሉ ጎን ለጎን በተካሄደ የሰብል ስብሰባ ስራም 5 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የነበረ ሰብል መሰብሰቡን ነው ያመለከቱት፡፡ ከሦስት ቀን በፊት በዘመቻ የተጀመረው የመከላከልና የሰብል ስብሰባ ሥራ ዛሬም ተጠናክሮ የቀጠል ሲሆን አመራሩ ሦስቱን ወረዳዎች ተከፋፍሎ እያስተባበረ መሆኑን አቶ አሊ አስረድተዋል፡፡ በአርጎባ ወረዳ የቀበሌ 04 ነዋሪ አርሶ አደር አብዱ ሸህ አሊ በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ያለሙት ማሽላ በአንበጣ እየወደመባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎችና ህብረተሰቡ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት ቢደርጉም ከአንበጣው ብዛት አንጻር ከአቅም በላይ እንደሆነባቸውና መንግስት አማራጭ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በቃሉ ወረዳ የቀበሌ 19 ነዋሪ አርሶ አደር ጀማል አደም በበኩላቸው በቀበሌያቸው አንበጣ ከተከሰተ ሦስት ቀን ማስቆጠሩን ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡና ተማሪዎች ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም የአንበጣ መንጋው ከአቅም በላይ በመሆኑ አንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት ማሽላ ሙሉ በሙሉ እንደወደመባቸው ተናግረዋል፡፡ በዘመቻው ከሚሳተፉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ወንድወሰን ኃይሉ "የአርሶ አደሩን ሰብል ከአንበጣ ለመታደግ ከትናንት ጀምሮ ድጋፍ እያደረኩ ነው" ብሏል። እንደተማሪ ወንደሰን ገለጻ የሚረብሽ ድምጽ በማሰማትና አንበጣውን በመጨፍጨፍ ከሚያደርጉት የመከላከል ሥራ በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ላይ ናቸው፡፡ በዘመቻ ስራው የወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ተማሪዎች፣ በየወረዳው ያሉ የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ህብረተሰቡና አርሶ አደሩ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም