መንግስት የሃገሪቱን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እናግዛለን.....የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች

57
ፍቼ ሰኔ 13/2010 የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስና ለሰላም መረጋገጥ  መንግስት የያዘውን አቋም በመደገፍ ለተፈፃሚቱም የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፍቼ ከተማ ነዋሪዎችና ምሁራን  ገለፁ ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ሪፖርትና ማብራሪያ በሃገሪቱ የተጀመረውን የመታደስ ሒደት እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል። በከተማው የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ማሞ በላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱን ችግሮች ገምግመው  የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ  ሰላም ፣አንድነትና እድገት ለማስመዝገብ የያዙት እቅድ ተስፋን የሰነቀ እንደሆነ ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለሕብረተሰቡ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መፍትሄ ለመስጠት ያላቸውንም ቁርጠኝነት የሚያመላክት እንደሆነም ገልፀዋል ። በየትኛውም ክልል የሚከሰት  የዘርና የብሄር ጥላቻን  በመፈተሽ በህግና ሥርዓት ለመመራት የተያዘውን አቋም ለማሳካት ከመንግስት ጐን ተሰልፈው የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስረድተዋል። የፍቼ ከተማ የቀበሌ04 ነዋሪ ወጣት አሸብር ኦልጅራ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱን ነባራዊ  ሁኔታ በማጤን መንግስት  የወሰደው እርምጃና ያስቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ወሳኝነት ያለው በሆኑ እደግፈዋለሁ" ብሏል። ይኸም በመራር ትግልና መስዋእትነት የተገኘውን  ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ከማስጠበቅ አልፎ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን ቅሬታዎች በመመለስ የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ ያስቀጥላል የሚል እምነት እንዳለውም አስታውቋል። በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን  ሴቶች  ሊግ ተወካይ  ወይዘሮ ዘውዲቱ አሰፋ እንደገለጹት በሃገሪቱ የታየው ሰላምና መረጋጋት እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይቅርታ መንፈስ እያስቀመጡት ያለውን መፍትሔ ይደግፋሉ። በተለይ ሕገ-መንግስታዊ  መብቶች በመላ ሃገሪቱ ተከብረው የሰላም ፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ትሩፋቶች ተጠቃሚ ለመሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ገልፀዋል ። የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭትን ጨምሮ በሀገሪቱ ህዝቦች መካከል የተንሰራፋውን የዘር ልዩነትና  የጥላቻ አዝማማያ ለማስቆም ህዝብና መንግስት መያዝ ያለባቸውን አቋም በግልፅ ያሳየ ንግግር በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል ። የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሴኔሳ ነጋሹ በኢትዮጵያ ታሪክ አስከፊ የሆኑትን  የጥላቻና የበቀል ታሪክ በመዝጋት አዲስ የይቅርታና የአንድነት መንፈስ እንዲሰርጽ የሚያነሳሳ በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡ ለሕዝብ ጥያቄና ቅሬታ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲቻልም የኢኮኖሚ ማሻሻያው ጉልህ እገዛ እንዳለው ገልጸው በተለይም ህዝቡን ለበለጠ አገልጋይነት የሚያነሳሳው በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ ችግሮችና የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ያለ ድብብቆሽ እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ አንድነት እንዲቀጥል የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም የሚያበረታታ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም