በሶስት ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው መንገድ ለስድስት ዓመታት ተጓትቷል

50
ነቀምቴ   ጥቅምት  25/2012  በምስራቅ ወለጋ ዞን በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ በ229 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው መንገድ ላለፉት ስድስት ዓመታት በመጓተቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታ አሰሙ ። በምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ የአርቁምቤ መንደር አንድ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ አስተራይ ደስታ እንደገለፁት የመንደር አስር-ዋጃ-ገሊላ ጠጠር መንገድ ግንባታ ከተጀመረ ስድስት ዓመታት አስቆጥሯል ። 57 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይኽው መንገድ ሊሙ፣ሐሮ ሊሙ፣ኢባንቱንና ጊዳ አያና ወረዳዎችን ለማገናኘት ተብሎ ግንባታው በ2005 ዓም ቢጀመርም ላለፉት ስድስት ዓመታት መጓተቱ ተገቢነት እንደሌለው አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል ። በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው መንገድ በስድስት ዓመታት እንኳን ማጠናቀቅ ያልተቻለበት ምክንያት እንቆቁልሽ እንደሆነባቸው ገልፀዋል ። መንገዱ የህዝብ ለህዝብ ግንኝነት በማጠናከር ፣ ምርትን ወደ ገበያ ለማቅረብና መጉላላትን ለማስቀረት ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ መንግስት ልተየ ትኩረት ሰጥቶ ለፍፃሜ እንዲያበቃው ጠይቀዋል ። በሊሙ ወረዳ የዳካ ቡሬ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉዓለም ቀነዓ በበኩላቸው የመንገዱ አለመጠናቀቅ በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር ወረዳን ከወረዳ ጋር እንዳንገናኝ እንቅፋት እየፈጠረብን ነው ሲሉ ብሶታቸውን ገልፀዋል ። ከመንገዱ አለመጠናቀቅ ጋር ተያይዞ በተለይም በክረምት ወቅት እናቶችና ሕፃናት ሲታመሙና በወሊድ ጊዜ የአምቡላንስ አገልግሎት ስለማያገኙ ህይወታቸው ለአደጋ የሚጋለጥበት አጋጣሚ እየተፈጠረ መሆኑን በምሬት ገልፀዋል ። በወረዳው የፍጥ ባቆ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሃብታሙ ፉፋ በሰጡት አስተያየት የአካባቢው ህዝብ ከስድስት ዓመት በፊት መንገዱ በፍጥነት እንዲሰራለት በመጓጓት ቤቱን በማፍረስና የእርሻ ማሳውን ጭምር ከቋሚ ተክሉ ጋር በመልቀቅ ለልማት እንዲውል መስጠቱን አስታውሰዋል ። በወቅቱ የተነቀሉ የቡና ችግኞች፣የባህር ዛፍና የተለያዩ ቋሚ ተክሎች እስከ ዛሬ ድረስ ቆይተው ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጥ እንደነበር በመግለፅ መንገዱ ባለመሰራቱ ደግሞ ሁለት ጉዳት እንደሆነባቸው አስረድተዋል ። የሊሙ ወረዳ መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ጉርመሳ አመኑ ስለሁኔታው ተጠይቀው የመንገዱ ግንባታ በመጓተቱ ምክንያት በህብረተሰቡ ዘንድ ቅረታ መፍጠሩን ገልፀው የፕሮጀክቱ ባለቤት የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን በመሆኑ በግንባታው ሒደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ አናሳ መሆኑን ተናግረዋል። የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን የኮንትራት አስተዳደር ባለሙያ ኢንጅነር ወንዱ ደሳለኝ በበኩላቸው የመንገዱ መጓተት በአከባቢው ህብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተቀብለውታል ። የኮንትራክተር አቅም ማነስ፣በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት በየጊዜው መቀያየርና የክትትልና ድጋፍ ውሱንነት እንዲሁም በቅርብ ጊዜ በአካባቢው የተከሰተው የፀጥታ ችግር ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸው አስረድተዋል ። በአሁኑ ጊዜ ከመንገድ ስራ ተቋራጭ ከሼድ ጀኔራል ኮንስትራክሽን ጋር የነበረውን ውል በማቋረጥ ወደ ሌሎች ተቋራጮች ለማስተላለፍ ጨረታ መውጣቱን በመግለፅ በአንድ ጊዜ ውስጥ ግንባታው ይጀመራል ብለዋል ። በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረው መንገድ ስድስት ዓመታት ቢያስቆጥርም የደረሰበት ደረጃ ከ60 በመቶ የዘለለ አይደለም ተብሏል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም