በወላይታ ሶዶ ለሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች የዞኑ አመራሮች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

49

ሶዶ (ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2012 በወላይታ ሶዶ ለሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች የዞኑ አመራሮች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እንዳሉት ድጋፉ የተገኘው በዞኑ በሁሉም የገጠርና የከተማ መዋቅሮች የሚገኙ ከ1 ሺህ 360 በላይ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመለገሳቸው ነው።

በዞኑ ጎልቶ የሚስተዋለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ መንግስት የጀመራቸውን ተግባራት ለማገዝ ሲሉ አመራሮቹ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የግብርና ማቀነባበሪያ፣ የወተት ተዋጽኦ ማምረቻ፣ የችፑድ እንዲሁም የብረታ ብረት፣ ቆርቆሮና ሚስማር ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም ከ22 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተለያዩ ተግባራዊ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

የሥራ አጥ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም "ማርጯ" የተባለ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ለማቋቋም ህጋዊ ሂደቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን አቶ ዳጋቶ አመልክተዋል።

በዞኑ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች አሟጦ ለመጠቀም የተደራጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

አቶ ዳገቶ አንዳሉት ባለፈው ሐምሌ ወር በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን የኢንዱስትሪዎችን ግንባታ ለማጠናቀቅም በአጠቃላይ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል።

በቀጣይም መላውን የዞኑን ነዋሪዎች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎችንና የግሉን ዘርፍ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና በውጭ ያሉ የዞኑን ተወላጆች በማንቀሳቀስ ገንዘብ ከማፈላለግ በተጨማሪ ለስራው ስኬታማነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ከህዝቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ድጋፍ ለማድረግ የአንድ ወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን የተናገሩት የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር ካንቲባ አቶ ጸጋዬ ሳሙኤል ናቸው።

በቀጣይ የህዝብ ተሳትፎን በማደራጀትና ውጤታማ በማድረግ የልማት ግቦች የተሳኩ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የዳሞት ወይዴ ወረዳ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢየሩሳሌም ዳዊት በበኩላቸው በአካባቢያቸው ያሉ የልማት አማራጮችን ለመጠቀም አሳታፊ አመራር መስጠትና አቅዶ መንቀሳቀሰ እንደሚገበ ገልጸዋል።

የዞኑ አስተዳደር የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች ያደነቁት ኃላፊው፣ በወላይታ የተጀመረው የኢንዱስትሪ ግንባታ ሥራ እንዲጠናቀቅ በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የግንባታ ሥራው ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተጀመረው የወላይታ ኢንዱስትሪ አብዮት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም