ሰላም ለማምጣትና ለማረጋጋት የአገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ ሚና መጫወት አለባቸው - የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

76
አዲስ አበባ ሰኔ 12 /2010 በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተጎዱ ዜጎችን ለማረጋጋትና ሰላም ለማውረድ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶችን መነሻ በማድረግ ከህዝቡ ጋር እየመከሩ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ትናንት ከቀትር በኋላ ወላይታ ሶዶ ከተማ በመገኘት ህዝብን አወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ለመግለጽ ጥቁር ለብሶ ከጠበቋቸው የሶዶ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ያካሄዱት ውይይት በስሜት የተሞላ ስለነበር  በዝግ እንዲሆን ተደርጓል። ውይይቱን የተከታተሉት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ህዝቡ የተሰማውን ሁሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስቷል። ህዝቡ ካነሳቸው ሀሳቦች መካከል የፈለጉበት ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት መብታቸው በመገደቡ፣ በክልሉ የእኩል ተጠቃሚነት መብት በመጓደሉ፣ እኩል የመልማት መብት በመነፈጋቸው፣ አድሎዓዊነት በመስፈኑ ለጉዳት ተዳርገናል የሚሉት ይገኙባቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሰጡት ማብራሪያ ችግሮች ቢኖሩም፣ በደሎች ቢደርሱም፣ ስህተትን በስህተት ለማረም ከመሞከርና ቂም በቀል ከማሰብ ይልቅ ለይቅርታ፣ ለአብሮነትና አንድነት መስራት የተሻለ መሆኑን አውስተዋል። ህዝቡ እንዲረጋጋ፣ ችግሮች ተፈተው መልካም ጉርብትናና አብሮነት እንዲቀጥል የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከፍ ያለ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋልም ብለዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ “እራሳቸውን ከፖሊቲካዊ አስተሳሰብና ከውግንና ማራቅ አለባቸው” ብለዋል። ህዝቡም የዘረኝነት አስተሳሰብና ዜጎችን እርስ በርስ በማጋጨት ርካሽ የፖሊቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ ኃይሎች ቦታ እንዲያጡ በቀድሞ መልካም ባህሉ፣ ወግና ስርዓቱ እንዲሁም እምነቱ ጸንቶ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመልካም አሰተዳደር፣ ለፍትህና የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎችን በተመለከተ ህዝቡ ከሃዘን ስሜት ሲወጣ በተረጋጋ መንፈስ ለማወያየት ቃል ገብተዋል። ትናንት የተካሄደው ውይይት ህዝቡን ከማረጋጋት አኳያ የተሳካ መሆኑን አቶ አህመድ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም