መገናኛ ብዙሀን በወልዋሎ ዓዲግራት ላይ እያስተላለፉት ያለው የዜና ዘገባ ሚዛኑን ያልጠበቀ ነው....የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ

145
መቀሌ ሚያዝያ 26/2010 መገናኛ ብዙሀን በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግርኳስ ቡድን ላይ እያስተላለፉት ያለው የዜና ዘገባ ሚዛኑን ያልጠበቀ ነው ሲል የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ቅሬታውን ገለጸ፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ነጋ አሰፋ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግላጫ ባለፈው ሰኞ ወልዋሎ ዓዲግራት ከመከላከያ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የተፈፀመው ጥፋት ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለውና ከቡድን መሪ የማይጠበቅ ነው፡፡ ክለቡ ለተፈፀመው ጥፋት ይቅርታ ከመጠየቁ በላይ በአምስት ተጫዎቾች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል። "ቡድኑ የራሱን የማስጠንቀቂያ እርምጃ ቢወስድም የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን ክለቡ የወሰደው እርምጃ ላይ ከማተኮር ይልቅ የተፈጠረውን ስህተት በተደጋጋሚ አጋኖ በማቅረብ በክለቡና በህዝብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ነው" ብለዋል፡፡ "ባለፉት ቀናት በተላለፉት የስፖርት ዜናዎች የክለቡ ስም በዘመቻ የማጥፋት ሥራ ነው የተካሄደው" ሲሉም አቶ ነጋ ገልጸዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሀኑ ዘገባ በጨዋታ ሜዳ ላይ የተፈጠረው ስህተትና ቡድኑ የወሰደው እርምጃን አገናዝቦ ካለመሰራቱ በተጨማሪ ለአንድ ወገን ያዘነበለና የስፖርት ተልዕኮን የሳተ መሆኑን ተናግረዋል። "አንድ የቡድኑ መሪ የፈጸመውን ጥፋት መገናኛ ብዙሀኑ ደጋግመው በማሳየትና ጥፋቱን ጠቅላላ የቡድኑ አባላት እንደፈፀሙት ተደርጎ በጅምላ ማቅረብ ፍትሃዊነት የጎደለውና ወገንተኝነት የተሞላበት ነው" ብለዋል። ይህ ድርጊት በእግርኳስ ዓለም ያልተፈጠረና ወልዋሎ ክለብ ላይ ብቻ የተፈጠረ አስመስሎ ማቅረብ የሀገሪቱን ስፖርት ጥላሸት የሚቀባ በመሆኑ ፈጥኖ ሊታረም እንደሚገባ ነው አቶ ነጋ የተናገሩት። የደጋፊን ሞራል በመንካት ቡድኑ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣና ፌደሬሽን በቡድኑ ላይ በሚወስነው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በ22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተገናኙበት ጨዋታ ላይ የመሀል ዳኛ የነበረው ኢያሱ ፈንቴ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረጻዲቅ ድብደባ እንደተፈጸመበት ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።
 
 
 
 
 
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም