በደቡብ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ደኢህዴን አስታወቀ

73
ሀዋሳ ሰኔ 12/2010 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ደኢህዴን/ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊና ክልላዊ የሰላምና የደህንነት ጉዳዮች ላይ አሰቸኳይ ስብሰባ አካሂዶ ውሳኔዎችን አስተላለፈ። ማዕከላዊ ኮሚቴው በሃዋሳ በወላይታ ሶዶና ወልቂጤ ከተሞች እንዲሁም በሲዳማ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ህይወታቸውን ላጡ፣ ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል፡፡ ለዘመናት አብረው የኖሩ፣ የጠነከረ የጋራ መስተጋብር የፈጠሩ፣ የመደጋገፍ የመተሳሰብና አብሮ ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌት የሆኑ ህዝቦች መካከል መታዬት ያልነበረት ተግባር መከሰቱንም ጠቅሷል፡፡ ጉዳዩ በፍጥነት መቀልበስ አለበት ያለው መግለጫው ክልሉን ወደተለመደው ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ በይደር መቆየት የሌለበት እንደሆነም አመልክቷል፡፡ የክልሉ ህዝብ ለዘመናት አብሮት የቆየውን የጋራ እሴቶች መደርመስ አይገባም፣ የሃዋሳ ህዝብና ክልሉ የመቻቻል የአብሮነትና የፍቅር ክልል መሆኑን እንደሃገር ያስመሰከረ እንደሆነም አንስቷል፡፡ “ከአንድ ሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በአንድ ክልላዊ አደረጃጃት ስር በመሆን በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበናል” ሲልም መግለጫው አመላክቷል፡፡ ደኢህዴን በዚህ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ከህዝቡ ጋር እየመከረ እየፈታ የመጣና በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበ ክልልና ድርጅት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ መታረም የሚገባቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን የገለጸው መግለጫው በጋራ ተወያይቶ የጋራ መፍትሄ መስጠት ብቸኛውና ትክክለኛው አቅጣጫ መሆኑን ድርጅቱ በጽኑ ያምናል ብሏል። የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ወቅት በዝርዝር ለውይይት የቀረቡ ጉዳዮችን ለመመለስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩም ተጠቅሷል፡፡ ማንኛውም ጥያቄ የግጭት መነሻ መሆን የለበትም ያለው መግለጫው በግጭት ወቅት የሚከሰተው የአካል መጉደል፣ ህይወት መጥፋትም ሆነ ንብረት ማውደምና ዘረፋ የክልሉን ህዝብ የማይመጥን ነው ብሏል። ክልላዊ ወቅታዊና የጸጥታና ደህንነት ሁኔታዎችን መነሻ አድርጎ የተወያየው የደኢህዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎች ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡ በዚህም ሃዋሳን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋት የእርስ በርስ ግጭትና በዚህ የሚጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት ውድመት በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት ወስኗል፡፡ ግጭቶች በተከሰተባቸው አካባቢዎች እየተባባሰ እንዳይሄድ ህዝቡ የራሱንና የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚገባውና የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር ጊዜ የማይሰጠውና ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑንም ስራ አስፈጻሚው ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ከኦሮሚያ አጎራባች ዞኖች ጋር የሚዋሰኑ የክልሉ አካባቢዎች በተለይም በጌዲኦ ዞን የተፈጠረውን የህዝብ መፈናቀል ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ድርጅቱ የጀመረውን ተግባር ከኦሮሚያ ክልልና ከፌደራል መንግስት ጋር ሆኖ እንደሚያጠናክርም ገልጿል፡፡ በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ባሉ የአማሮና ቡርጂ ወረዳዎች የሚታየውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግስታት ጋር በመሆን ልዩ ትኩረት እንደሚያደርግ ስራ አስፈጻሚው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የህግ የበላይነትን ማስከበርና የህዝቡን ደህንነት የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት በከፍተኛ የህዝባዊነት እንዲንቀሳቀሱ አሳስቧል፡፡ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት በየአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮችን በድርጅቱ መርህ ላይ ቆመው በድርጅታዊ ዲሲፕሊን ለመፍታት እንዲንቀሳቀሱ ድርጅቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም