ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ የምዕራብ ጉጂ ዞን የእምነትና ባህላዊ መሪዎች ተናገሩ

84

ዲላ ጥቅምት 24 ቀን 2011 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዕውቀት መቅሰሚያ እንጂ፤ የፖለቲካ መድረኮች ባለመሆናቸው ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ የምዕራብ ጉጂ ዞን ታዋቂ የእምነትና ባህላዊ መሪዎች አስገነዘቡ

የዞኑ አባገዳዎች፣ የሐይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በሰላም ዙሪያ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

መሪዎቹና የአገር ሽማግሌዎቹ በዚሁ ወቅት እንዳሳሰቡት ተማሪዎቹ ተቋማቱ የዕውቀት ማስተላለፊያና ማሸጋገሪያ መድረኮች መሆናቸውን በመረዳት ዕውቀት መገብየት ይጠበቅባቸዋል።

አባገዳ ዳንቦብ መልካ ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ለትምህርታቸው ትኩረት መስጠት  እንደሚኖርባቸው አመልክተው ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እንዲተጉም በማሳሰብ፡፡

ቄስ በቀለ አኖሌ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት የተረጋጋና ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑን ሰላማዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ በመማር ማስተማር ሂደት  እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮች አስቀድሞ በመለየት ማስተካከያ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሰላምና መረጋጋት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም  በምርምርና ጥናት ተወዳዳሪና ግንባር ቀደም ለማድረገም ትኩረት መሰጠቱን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አንዳንድ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት መድረኩ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲያጎለብቱ እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል።

የትምህርት ዘመኑን የተረጋጋና ሰላማዊ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሚና ከመወጣት በተጓዳኝ በትምህርታቸው ላይ ብቻ ለማተኮር  ውጤታማ ለመሆን  እንጥራለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም