አርሶ አደሮቹ በአንድ የምርት ዘመን በተደጋጋሚ እያመረቱ ነው

95
አሶሳ ጥቅምት 24/  2012 . የቤንሻንጉል ጉሙዝ አርሶ አደሮች አስፈላጊውን ግብአት በመጠቀምና በአንድ የምርት ዘመን በተደጋጋሚ በማምረትና ኑሮአቸውን ማሻሻል እንደቻሉ ገለፁ ። በአሶሳ ዞን የ19 ቤተሰብ አስተዳዳሪና የቤልሜሊ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሸህዲን ሙስጣፋ እንደገለፁት በዘንድሮው የመኸር አዝመራ ሶስት ሄክታር መሬት አልምተው ምርታቸውን ለመሰብሰብ በዝግጅት ላይ ናቸው ፡፡ በክረምቱ መግቢያ ላይ የዘሩትን በቆሎ በቁሙ እሸት በመሸጥ ከ30 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል ፡፡ ምርቱን ባነሱበት ቦታ ላይ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሽምብራና ጤፍ በመዝራት በአሁኑ ወቅት አዝመራው በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል ። በጥምር ግብርና የተሻሻሉ የስኳር ድንች፣ ለውዝ፣ አኩሪ አተር ፣ ማሽላ፣ ኑግና ሌሎች ሰብሎችን በመዝራት ከአምናው የተሻለ ምርት በመጠቀም ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል ። የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ጊዳዳ ማህጁብ በበኩላቸው ካለሙት ሁለት ሄክታር መሬት 30 ኩንታል በቆሎና 20 ኩንታል አኩሪ አተር እንደሚሰበስቡ አርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ከዘሩት በቆሎ ካለሙት ምርት በቅርቡ የሚሰበሰብ ሲሆን በቆሎ 30 ኩንታል እንዲሁም አኩሪ አተር ደግሞ 20 ኩንታል የሚጠጋ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ አድረገዋል፡፡ ምርቱን እንደሰበሰቡ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ በርበሬና ሌሎችን ተክሎችን ለማምረት ችግኝ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ መስጣፋ መርቀኔ የተባሉ አርሶ አደር አንዳሉት ደግሞ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ማሽላ ከፍተኛ ምርት ወደ ጎተራ ማስገባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ምርት ያገኙበት የማሽላ አገዳ ድጋሚ እንዲያቆጠቁጥ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረጋቸው ሁለተኛው ዙር ምርት ለመስጠት የሚያስችል ፍሬ መያዙን አስረድተዋል ። አስተያየት ሰጪ አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት የውጤታማነታቸው ምስጢር የግብርና ባለሙያዎችን ምክር ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ ጠንክረው በመስራታቸው ነው፡፡ የክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ እንደገለፁት ቢሮው በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ ከያዛቸው አቅጣጫዎች አንዱ ዋነኛው የውጤታማ አርሶ አደሮችን ተሞክሮ ማስፋፋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የአርሶ አደሩ ሕይወት መሻሻል በቁርጠኝት የሚደግፉ የቀበሌና የወረዳ አመራሮች መኖርና የባለሙያዎች ድጋፍ ለምርታማነቱ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ። የክልሉ አርሶ አደሮች ከምንም በላይ ከድህነት የሚላቀቁት በራሳቸው ጥረት እንደሆነ ከሞዴል አርሶ አደሮች ሕይወት ሊማሩ እንደሚገባም አቶ ሙሳ አስገንዝበዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም